Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የጀመረው ምክክር በጋራ መሥራትን እንደሚያዳብር ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚያደርጋቸው የምክክር መድረኮች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን እንደሚያበረታታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

ከዚህ ቀደም የሀገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ብዙ ችግሮች ያሉበትና የመወያየት ባህል ያልዳበረበት እንደነበር የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ግን መንግሥት የዴሞክራሲ ባህልን ለማጎልበት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ ለመሥራት የጀመራቸው ተግባራት አበረታች ናቸው ብለዋል።

የፌደራልና የክልል መንግሥታት በሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ፣ የልማት፣ ሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ገንቢ ምክክር ማድረጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፖለቲካ ፓርቲ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ያደረጉት ምክክር በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን በማጠናከር ጉልህ ጠቀሜታ አለው ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ከመንግሥት ጋር በየደረጃው የሚያደርጉት ምክክር የሚና ግልጽነትን በመፍጠር ለሚያጋጥሙ ሀገራዊ ችግሮች በጋራ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስችል አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.