ከብሔራዊ ባንክ አዲሱ መመሪያ መተግበር በፊት ምዝገባ አከናውነው ተቀባይነት ያገኙ ሠነዶች በነበረው የምንዛሪ ተመን ይቀጥላሉ – ጉምሩክ ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረበት ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በፊት የሠነድ ምዝገባቸው የተከናወኑ እና ተቀባይነት ያገኙ ሠነዶች በበፊቱ የምንዛሪ ተመን እንደሚቀጥሉ የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በሰጡት መግለጫ÷ ተቋማቸው የሠነድ ምዝገባ እና ማጣራት ሂደቱን በአግባቡ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ብሔራዊ ባንክ አዲሱን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረበት ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በፊት የሠነድ ምዝገባቸው የተከናወኑ እና ተቀባይነት ያገኙ ሠነዶች በበፊቱ የምንዛሪ ተመን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ የቀረቡ ሠነዶች ያልተሟሉ እና ቀሪ ጉዳዮች ኖረው ተቀባይነት ያላገኙ ሠነዶች የሚስተናገዱት በዕለቱ የምንዛሪ ተመን መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለው የአሠራር መመሪያ መሠረት የገቢ ዕቃዎችን ሠነድ በመፈተሽ ወደ ሀገር እንዲገቡ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በምንዛሪ ግብይቱ ላይ ባለው ለውጥ ምክንያት የተለያዩ ጥያቄዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ ከሕግና መመሪያ ውጭ የተሠራም ሆነ የሚሠራ ሥራ አለመኖሩን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ የሥራ መመሪያዎቹን ለደንበኞቹ የማሣወቅ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ በአሠራር ሂደት ያሉ ጉዳዮችን ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
በሰለሞን ይታየው