Fana: At a Speed of Life!

ጊኒ ለአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ትግበራ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጊኒ ለአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ትግበራ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ የኢኳቶሪያል ጊኒ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ማሪ ክሩዝ ኤቩና አንደሜ አስታወቁ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ማሪ ክሩዝ ኤቩና አንደሜ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያና ኢኳቶሪያል ጊኒ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸውና ግንኙነቱ በመሪዎች ደረጃም የተሳሰረ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና ሁሉን አቀፍ ትብብር ለመመሥረት የሚያስችል የፖለቲካ ምክክር መድረክ ማዘጋጀት እንደሚገባ ከኢኳቶሪያል ጊኒ አቻቸው ጋር ተስማምተዋል።

የኢኳቶሪያል ጊኒ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ማሪ ክሩዝ ኤቩና አንደሜ በበኩላቸው ፥ ሁለቱ ሀገራት መልካም ግንኙነት እንዳላቸው በመግለጽ በአፍሪካ ውስጥ በተለያዩ መስኮች በጋራ የሚሠሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ሀገራቸው ለአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ትግበራ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በጠንካራ ትብብር እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ኢኳቶሪያል ጊኒ በቀጣይ በሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት የሕብረቱ የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ዕጭ ተወዳዳሪ ማቅረቧን እንደነበር ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.