Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ሃይል የማመንጨት አቅሟን ወደ 13 ሺህ ሜጋ ዋት ልታሳድግ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2028 የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅሟን ወደ 13 ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ ማቀዷን ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ ታንዛኒያ በተካሄደው የአፍሪካ ታዳሽ ሃይል ጉባዔ የፓናል ውይይት ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ÷ ኢትዮጵያ በቀጣናው የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነትን ለማስፋፋት በትኩረት እየሰራች ነው፡፡

በ2028 ከታዳሽ ሃይልና ከተለያዩ ምንጮች የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅሟን ወደ 13 ሺህ ሜጋ ዋት ለማሳደግ ማቀዷንም አስረድተዋል፡፡

በዚህም 14 ሀገራትን በኤሌክትሪክ ሃይል የማስተሳሰር እቅድ ይዛ በትብብር እየሰራች መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለጅቡቲ፣ ኬንያና ሱዳን የኤሌክትሪክ ሃይል እያቀረበች መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በቅርቡ የምስራቅ አፍሪካ ኤሌክትሪክ ሀይዌይ ፕሮጀክት አካል የሆነው ሃይል ከኬንያ ወደ ታንዛኒያ የሚያስተላልፈው መስመር የሙከራ የሃይል አቅርቦት መጀመሩ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.