የአዲስ አበባ የለውጥ ጉዞ አስደንቆኛል – ዌላርስ ጋሳማጌራ
አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ በአስደናቂ የለውጥ ጉዞ ላይ እንደምትገኝ መመልከታቸውን የሩዋንዳ ፓትሪዮቲክ ፍሮንት (አር ፒ ኤፍ) ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ዌላርስ ጋሳማጌራ ገለጹ።
በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ለመታደም አዲስ አበባ የሚገኙት ዌላርስ ጋሳማጌራ፤ የአንድነት ፓርክን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው አዲስ አበባ በለውጥ ጉዞ ላይ መሆኗን መመልከታቸውን ተናግረው፤ ኢትዮጵያ ተራማጅ ሀገር ናት ብለዋል።
አዲስ አበባን ውብና ጽዱ ለማድረግ የተደረጉ ስራዎችን አድንቀው፤ በቀጣይም ሌሎች አካባቢዎችን እንደሚጎበኙ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የአንድነት ፓርክ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ሀገርነት የሚገልጥ ብቻ ሳይሆን ያለፈን ታሪክ ከዛሬ ጋር አስተሳስሮ በትንሽ ቦታ የሚያሳይ ድንቅ ስፍራ ሆኖ እንዳገኙት ጠቁመዋል።
የጥንታዊ ታሪክ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶችን በማልማትና በመጠበቅ በዘርፉ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የጀመረችውን ጥረት አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ ተሞክሮ ቅርሶችን ለመንከባከብ ዘርፈ ብዙ ስራ እያከናወነች ላለቸው ሩዋንዳ ወሳኝ ልምድ የሚቀሰምበት እንደሆነ ገልጸዋል።