Fana: At a Speed of Life!

አቶ አደም ፋራህ ከኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ ልዑክ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ከኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ የልዑካን ቡድን አባላት ጋር ተወያዩ፡፡

በዚሁ ወቅት አቶ አደም የኢትዮ-ኩባ ታሪካዊ ግንኙነትን አውስተው፤ በአሁኑ ጊዜ በብልፅግና ፓርቲ መሪነት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች እጅግ ውጤታማ ስኬቶች እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አምስት ሀገራት አንዷ መሆኗን፣ ምጣኔ ሀብቱ ባለፈው ዓመት በአማካይ በ8 ነጥብ 1 በመቶ ማደጉን፣ በዚህ ዓመትም በ8 ነጥብ 4 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ አንስተዋል።

ፓርቲው የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማሳካት በአምስት ዘርፎች በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሆነ ያብራሩት አቶ አደም፤ በተለይም በግብርናው መስክ  በስንዴ ምርት እምርታዊ ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።

በጤና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተሻለ ስራ ለማከናወን ከኩባ ጋር ትብብራቸው እንደሚጠናከር ገልፀው፤ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነትና የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።

የልዑኩ መሪ የኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ዩዲ ሜርሴዲስ ኸርናንዴዝ በበኩላቸው፤ በሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ላይ ፓርቲያቸው እንዲሳተፍ ስለተጋበዘ አመስግነዋል፡፡

ሀገራቱ በኢንቨስትመንት፣ በዲፕሎማሲ እና በሌሎች መስኮች ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል ማለታቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ አመላክቷል፡፡

የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነትን በማጠናከር የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ያላቸውን የጋራ ታሪክ የሚያጠናክር፣ ዕድገታቸውንም የሚያጎለብቱ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.