Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያውያንን ያለ ልዩነት ያቀፈ ህብረብሔራዊ ፓርቲ ነው – አቶ አደም ፋራህ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልፅግና ፓርቲ ሁሉም ኢትዮጵያውያንን ያለ ልዩነት ያቀፈ እውነተኛ ህብረብሔራዊ ፓርቲ ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡

‘ከቃል እስከ ባህል’ በሚል መሪ ሀሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄደው የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ነው።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንቶችና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የጎረቤት ሀገራት እህት ፓርቲዎች እና የብሪክስ አባል ሀገራት እህት ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመድረኩ አቶ አደም ፋራህ ብልፅግና ፓርቲ ሚዛናዊነትን እና አስተሳሳሪ ትርክትን መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያሉትን ተቃርኖዎች የሚያስታርቅ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ብለዋል።

ፓርቲው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ አልሞ የተቋቋመ ፓርቲ ነው ብለዋል፡

ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግም ሁሉም ኢትዮጵያውያንን ያለ ለዩነት ያቀፈ እውነተኛ ህብረብሄራዊ ፓርቲ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ፓርቲው ሁሉም ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በፍትሐዊነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የዲሞክራሲ ባህልን ማጎልበት እና የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴትን ማዳበር ወሳኝ መሆኑንን አምኖ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው ለህዝብ የተገባው ቃል የደረሰበት ደረጃ የሚገመገምበት እንደሚሆን ገልጸው፤ በበርካታ ድሎች ታጅበን በምናካሂደው በዚህ ጉባኤ በርካታ አቅጣጫውችና ውሳኔዎች የሚወሰኑበት መድረክ ይሆናል ብለዋል::

ቃል በገባነው መሰረት የስንዴን ምርት ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ መላክ የጀመርንበት፣ በርካታ ሰው ተኮር ስራዎችን ሰርተናል ብለዋል::

በጉባኤው ለመሳተፍ ከተለያዩ ሀገራት ለመጡ እህት ፓርቲዎች አመራሮችም ምስጋና አቅርበዋል።

እንደ ፓርቲ ቃልን በተግባር የማረጋገጥ ባህል መሰረት ህዝቡን በማሳተፍ ተግዳሮቶችን በብቃት ተሻግረን ከእዳ ወደ ምንዳ ለመሻገር ጥንካሬ እና ጉድለታችንን እየለየን ጎዶሎውን እየሞላን ፈተናን ወደ እድል እየቀየርን ለዛሬ እና ለነገ ትውልድ ዘላቂ መብት ጥብቅና ቆመን ለእምርታዊ እድገት እየተጋን ለዚህ በቅተናል ሲሉም ገልፀዋል፡፡

የድህረ አንደኛ ጉባዔ ዓመትታ በተገባው ቃል መሰረት በአረንጓዴ አሻራ፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመገባደድ ዋዜማ ላይ መድረስ፣ ዘመናዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማትና የነበሩትን መጠገን ከተመዘገቡ ድሎች መካከል እንደሚገኙበት አንስተዋል።

እንዲሁም የፅንፈኝነትን እና ዋልታ ረገጦችን አመኬላ በዘላቂነት ለመንቀል የሚያሥችሉ ውጤታማ የሀገር ግንባታ ስራዎችን የሰራንበት፣ በርካታ ሰው ተኮር ስራዎችን የሰራንበት፣ ከፍተኛ የድህነት ቅነሳ እና የስራ እድል ፈጠራ ስራዎችን የሰራንበት ነበር ብለዋል።

ስኬቶቹን ዘላቂ ለማድረግና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለማለፍ ሰፋፊ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ ፓርቲውን በአደረጃጀት፣ በአሰራርና በፋይናንስ የሚያጠናክሩ ስራዎችን መሰራታቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም በአመራርና በአባላት ማጥራት ስራ ተጨባጭ ለውጥ አምጥተናል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ ጉባዔ ፓርቲያዊ ቁመና ተመርምሮ ትናንትን ዛሬንና ነገን የሚያስተሳስሩ ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ ጠቁመዋል።

 

በፌቨን ቢሻውና የኔወርቅ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.