Fana: At a Speed of Life!

ከፊታችን ዓርብ ጀምሮ የፖሊዮ ክትባት መሰጠት ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመጀመሪያ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከየካቲት 14 እስከ 17 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ክትባቱ የሚሰጠው ድሬዳዋ አሥተዳደርን ጨምሮ በትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ሐረሪ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዘመቻውም ከ13 ነጥብ 8 ሚሊየን ለሚልቁ ሕጻናት ክትባቱን ለመስጠት መታቀዱን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የፖሊዮ ወረርሽኝ ምላሽ አስተባባሪ ሚኪያስ አላዩ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡

ለመጀመሪያው ዙር የክትባት ዘመቻም ከ84 ሺህ 890 በላይ የጤና ባለሙያዎች ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በመደበኛ የክትባት መርሐ-ግብር ተደራሽ ያልሆኑ ወይም ጀምረው ያቋረጡ ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን በመለየት ክትባት የመስጠት ሥራ ከዘመቻው ጎን ለጎን እንደሚከናወንም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም ቆልማማ እግር ችግር ያለባቸውን ልጆች የመለየት ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ያላቸው ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ልጆቻቸው ከዚህ በፊት የፖሊዮ ክትባት ቢከተቡም ባይከተቡም በዘመቻው እንዲያስከትቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በትዝታ ደሳለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.