አቶ ኦርዲን የጀጎል ቅርስ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት የጎብኚዎችን ቁጥር መጨመሩን ገለጹ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጀጎል ቅርስ የተከናወነው የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት የቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል።
በመድረኩ የአፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ በክልሉ በቅርስ ጥበቃ እና ልማት ዘርፍ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል።
በተለይ በዓለም አቀፉ የጁገል ቅርስ ላይ የተከናወነው የመልሶ ልማት ስራ ቅርሱን ለጎብኚዎች እና ነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ማስቻሉን ጠቅሰው÷ ይህም በቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትን በመፍጠር የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲጎለብት ማድረጉን ተናግረዋል።
የክልሉን ቋንቋ ከማሳደግ አንፃር የተጀመሩ አበረታች ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል የሐረሪ ክልልን በኮሪደር ልማት ፅዱ፣ ውብ እና በስርዓት የምትመራ ምቹ ከተማ ለማድረግ እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎች አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ በተከናወኑ ሰፋፊ የልማት ስራዎች የተመዘገቡ ውጤቶች የአመራሩ እና የህዝቡ ጠንካራ የቅንጅት ስራ ውጤቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ መንግስት የተከናወኑ ጠንካራ ስራዎችን በማስቀጠል እና ክፍተቶችን ለማረም በመስማማት የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባውን ማጠናቀቁን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡