በአማራ ክልል ከተሞችን ዘመናዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከተሞችን ዘመናዊ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ አስታወቁ፡፡
የከተማና መሠረት ልማት ሚኒስቴር አመራሮች በተገኙበት፤ የክልሉን ከተሞች የበጀት ዓመቱን አጋማሽ ዕቅድ አፈጻጸም መገምገማቸውን ርዕሰ መሥተዳድሩ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
የዘርፉን ተቋማት በማስተሳሰርና ማሕበረሰቡን በማሳተፍ የከተሞችን ጥራትና ደረጃ ለማሻሻል በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል፡፡
በክልሉ በሰባት ከተሞች የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች አበረታች ውጤት እያሳዩ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይም የክልሉ መንግሥት የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በማጠናቀቅ፤ ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋት አቅዷል ብለዋል፡፡
የክልላችን ከተሞች በፕላን የሚመሩ፣ ዘመናዊነትን የተላበሱ፣ ለኑሮ ምቹ፣ ጽዱ፣ ውብና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
የአማራ ክልል ከተሞች የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ማሳለጫ፣ የምርት፣ የንግድና የገበያ ማዕከልንታቸው በይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት በቅንጅትና በትጋት እንደሚሠራ ገልፀዋል፡፡