ክልሉ በመሬት መንሸራተት ጉዳት እንዳይደርስ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የበልግ ወቅትን ጨምሮ በመጪው ክረምት የሚኖረውን ዝናብ ተከትሎ በጎርፍ፣ መሬት መንሸራተትና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች በሰው ሕይዎትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስታወቀ፡፡
የክልሉ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እንድሪስ ኤርሚያስ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ባለፈው ዓመት በሥምንት ዞኖች በ149 ሺህ 780 ወገኖች ላይ መፈናቀልን ጨምሮ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሷል፡፡
ለእነዚህ ወገኖችም ከጊዜያዊ ሰብዓዊ ድጋፍ እስከ ዘላቂ ማቋቋም የደረሰ ሥራ መከናወኑን አረጋግጠዋል፡፡
በዚሁ መሠረት በጎፋ፣ ወላይታ፣ ጋሞ እና ኮንሶ ዞኖች የተለያየ ቁጥር ያላቸው መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውን እና ለተጎጂዎች መተላለፋቸውን እንዲሁም በግንባታ ላይ ያሉ እና ለመገንባት የቦታ ርክክብ የተደረገባቸው መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡
አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መልሶ ማቋቋም ሥራን በተመለከተም፤ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሠነች ወረዳ ትምህርት ቤቶች፣ የሰውና የእንስሳት ጤና ኬላ ግንባታ መሠራቱን፣ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ የሰውና የእንስሳት ጤና ኬላ፣ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋምና የውኃ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በዚህ ዓመት እንዳለፈው ዓመት አይነት ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ተጋላጮችን በመለየት በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ከክልል እስከ ወረዳ ግብረ-ኃይል መዋቀሩንና እስከ ቀበሌ ድረስ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክር ቤት መኖሩን አስረድተዋል፡፡
በተቋማት ደረጃም ዘንድሮ በጎርፍና መሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት እንዳይደርስ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በክልሉ ካሉ 12 ዞኖች በሥምንቱ የተወሰኑ ወረዳዎች ከፍተኛ መጠን ያለውን ዝናብ ተከትሎ ለጎርፍ እና መሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭነት መኖሩን አስገንዝበዋል፡፡
በክልሉ በያዝነው የበልግ እና የክረምት ወቅቶች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሥርጭት ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ይህንን ተከትሎ በተጋላጭ ጋሞ፣ ጎፋ እና ወላይታ ዞኖች ትኩረት ተሰጥቶ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይም ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖችም የውኃ መፋሰሻ በማዘጋጀት እና የዘወትር እንቅስቃሴዎቻቸውንም ጥንቃቄ በተሞላበት አግባብ እንዲከውኑ አሳስበዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው