Fana: At a Speed of Life!

ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ የሠራተኞች ሁለንተናዊ ክህሎትና ጥረት ወሳኝ ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለሁለንተናዊ ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ በምሰሶነት የተለዩት የምጣኔ ሀብት ዘርፎች የሠራተኞችን ሁለንተናዊ ክህሎትንና ጥረት የሚጠይቁ መሆናቸውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

አገልግሎቱ ለሠራተኞች ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

በመልዕክቱም ፈጠራና ፍጥነት የታከለበት የክህሎት ግንባታ ቀጣይነት ላለው የሥራ እድል ፈጠራና ዋስትና ወሳኝ መሆኑን ገልጿል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ፈጠራና ፍጥነት የታከለበት የክህሎት ግንባታ ቀጣይነት ላለው የሥራ እድል ፈጠራና ዋስትና ወሳኝ ነው

“በአምራች ኢንዱስትሪዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምቹ የሥራ ሁኔታ ለማህበራዊ ፍትህ” በሚል መሪ ቃል

ኢትዮጵያ የዓለም የሠራተኞች ቀንን የምታከብረው የኢንዱስትሪ ሰላምን፣ የሥራ ላይ ደኅንነትንና የሠራተኞችን ክሕሎት ማሳደግን ልዩ ትኩረት በመስጠት ነው፡፡

ወደ ብልጽግና የሚደረገዉ ጉዞ ያለ ኢንዱስትሪ ሰላም፣ ያለ ሠራተኞች የሥራ ላይ ደኅንነት እና ዘመኑ የሚጠይቀዉን ክሕሎት ለሠራተኛዉ ሳያስታጥቁ የሚታሰብ አይደለም፡፡

በመሆኑም በዓሉን ስናከብር ሠራተኞች፣ የሠራተኛ ማኅበራት እና የክህሎት ሥልጠና ተቋማት ለኢንዱስትሪ እና አገራዊ ሰላም እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ ዕውቅና በመስጠት፣ አሠሪዎች ደግሞ ለሠራተኞች የሚፈጥሩትን ምቹ የሥራ አካባቢ እና የሥራ ላይ ደኅንነት በማበረታታት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለሁለንተናዊ ብልጽግና ለምታደርገዉ ጉዞ በምሰሶነት የተለዩት የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ማለትም ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ኢኮኖሚ የሠራተኞችን ሁለንተናዊ ክህሎትንና ጥረት የሚጠይቁ ናቸው፡፡

ይህንን ታሳቢ በማድረግም መንግሥት ኢንዱስትሪዎች በብዛት የሚፈልጓቸዉን በመካከለኛ ደረጃ የሠለጠኑ ሠራተኞች ለማቅረብ ሰፋፊ የክሕሎት ሥልጠናዎችን በቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና በተለያዩ አማራጮች እያቀረበ ይገኛል፡፡

የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ለዚህ አንዱ አብነት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

መርሐ ግብሩ ሠራተኞች ለአሁኑና ለቀጣዩ ዲጂታላይዝድ ዓለም ብቁ የሚያደርጋቸውን አቅም የሚገነባ ሲሆን ከዓለም እውቅ የኦንላይን ሥልጠና ማዕከል በነጻ የሚሰጡ አራት የሥልጠና መስኮችን የሚያካትት ነው።

የሥራ ፈጠራንና ለሥራ ፈጠራ ምቹ የሆነ ምህዳር መፍጠር የመንግስት ዋነኛ ትኩረቶች መካከል ሲሆን ከዚህ አንጻር በዚህ ዓመት በሁሉም የኢኮኖሚ መስኮች ከሦስት ሚሊዮን በላይ ስራዎች ተፈጥረዋል።

ዜጎች መብታቸው ተጠብቆ በውጭ ሃገራት ሥራዎች እንዲሰማሩ ለማድረግ መንግስት ከመዳረሻ ሃገራት መንግስታት ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት ከ340ሺህ በላይ የውጭ ሃገር የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ቴክኖሎጂ የፈጠረውን አስቻይነት ሚና በማስፋት ከ45ሺህ በላይ የርቀት ስራዎች (remote jobs) ተፈጥረዋል።

እንዲህ አይነት አዳዲስ የሥራ ፈጠራ መስኮች እንዲስፋፉ ዜጎች በመንግስት የሚመቻቹ እንደ የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ አይነት የሥልጠና እድሎችን እና ሌሎች በግል ጥረት የሚገኙ የአቅም መገንቢያ መንገዶችን በመጠቀም ራሳቸውን ብቁ ማድረግ ይጠበቃል።

ይህን ለማሳካት በተለያየ ደረጃ ያሉ በርካታ የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ ጥረትን የጠየቀ ቢሆንም ካለው ፍላጎት አንጻር ተጨማሪ ስራዎች እንደሚጠበቁ መንግስት ይገነዘባል።

ለዚህም ፈጠራና ፍጥነት የታከለባቸው የፖሊሲና የተግባር ምላሾች ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል።

በዚህ አጋጣሚ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት፣ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሠራተኛ ማህበራት እና ሌሎችም ባለድርሻዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪውን ያስተላልፋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.