ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡የግብርና ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት ያለፉት ዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንዳሉት÷በበጀት ዓመቱ 30 ሚሊየን ሄክታር በዘር በመሸፈን ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራትም 31 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር በዘር መሸፈኑን ጠቅሰው÷ በዚህም እስካሁን ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
1 ነጥብ 1 ሚሊየን ቶን ቡና መመረቱን የገለጹት ሚኒስትሩ÷300 ሺህ ኩንታል ቡና ለውጪ ገበያ በማቅረብ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን ከ300 ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት መሰብሰቡን ገልጸው÷የበጋ መስኖ ስንዴን የመሰብሰቡ ሒደት አለመጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የግብርናው ዘርፍ በምርታማነት እና እሴት በመጨመር ረገድ የተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ እድገት ያሳየ መሆኑን ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በይስማው አደራው