በፍትሕ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን ትግበራ የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል – አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፍትሕ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን ትግበራ የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች እና የፍትሕ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን አተገባበርን ገምግሟል።
አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷የፍትሕ ተቋማትና ፍ/ቤቶች የሕዝብ አመኔታ ያለው ተቋም መገንባት እና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ከ2016 ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የፍ/ቤቶች ፍኖተ ካርታና የፍትሕ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ተስፉ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት መስራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት በበኩላቸው÷ የፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
በተለይ የቅጣት አወሳሰን መመሪያን በቅርቡ ወደ ሥራ ለማስገባት የተከናወነውን ተግባር ለአብነት አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም የፍርድ ቤቶች ሥራን ውጤታማ ለማድረግ ባለፉት 9 ወራት በርካታ ተግባራት የተከናወኑ መሆኑን አንስተው÷ ዲጂታላይዝ መደረጉ የመዝገብ መጥፋት ችግርን ማስቀረት መቻሉን አንስተዋል፡፡
የፍትሕ ዘርፉን በተፈለገው ደረጃ ውጤታማ ለማድረግ እና ለማስቀጠል በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡