የኢትዮጵያና ሩሲያ የንግድ ግንኙነት እያደገ መጥቷል – አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ገለጹ።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ለሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ልማት እና ዓለም አቀፍ ትብብር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የገለጹት አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን፤ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገርም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የግንኙነት መድረክ ያላትን ታሪካዊ ሚና የበለጠ ያጠናክራል ብለዋል።
በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መሠረት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
የሩሲያ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የገበያ አቅም በመረዳት በኢነርጂ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በግብርና ዘርፎች ለመሰማራት እንደሚፈልጉም አመልክተዋል።
አዳዲስ የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እየተሰማሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በዚህም የሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የበለጠ እያደገ መምጣቱን ማስረዳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በአሁኑ ወቅት የኢኮኖሚ ትብብራቸው ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው፤ በፈረንጆቹ 2024 የመጀመሪያዎቹ 10 ወራት የነበራቸው የንግድ ልውውጥ በ40 በመቶ መጨመሩን አስታውሰዋል።
በአውቶሞቲቭ ማምረቻ፣ በኢነርጂ ልማት፣ በኤሌክትሪክ ቁሳቁስ፣ በኬሚካል ምርቶች፣ በምግብ ማቀነባበሪያ፣ የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ የንግድ ውክልና በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያሉትን ዕድሎች ለመጠቀም ከሚፈልጉ ኩባንያዎች ጥያቄዎችን እየተቀበለ መሆኑንም ገልጸዋል።
የሀገራቱን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ መሰማራት ለሚፈልጉ የሩሲያ የንግድ ድርጅቶች ሰፊ ዕድሎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡