Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያን ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያን ለመተግበር የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው  ምክትል ሀላፊ አቶ ዳምጠው ገመቹ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለፁት÷ የተቋማት አገልግሎት በተሟላ መልኩ ውጤት እንዲያመጣ የመንግስት ሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ አቅጣጫን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ማሻሻያው ከመተግበሩ በፊት ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የመመለስ፣ የስነ ምግባር ችግሮችን የማረምና ማስተካካል እንዲሁም ተቋማትን እና አገልግሎታቸውን የመለየት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በክልሉ ትላልቅ ከተሞች የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

የሰራተኛና አመራሮችን ብቃትን ለመለየት ውጤትን መሰረት ያደረገ ምዘና እንደሚደረግ ገልፀው፤ የተሻለ አፈፃፀም ለሚያስመዘግቡ ዕውቅና በመስጠት ተቋማት በአዲስ መልክ ሥራ እንደሚጀምሩ አመላክተዋል፡፡

ችግሮች ከተቋም ግንባታ እንደሚመነጩ ጠቅሰው÷ ዘመናትን የተሻገርንበት ውጣ ውረድ የበዛበት አሰራር ለመቅርፍ  ማሻሻያው ተስፋ ተጥሎበታል ብለዋል፡፡

ማሻሻያው ሲተገበር መሰረታዊ ለውጥ እንደሚጠበቅ በመግለጽ፤ የህዝብና የሀገርን ፍላጎት ማሟላት የሚችሉ ተቋማትን መገንባት የማሻሻያው ዋና አላማ መሆኑን ተናግረዋል።

ህዝቡን የሚያማርሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በማሻሻያው እንደሚቀረፉ የተናገሩት ም/ኃላፊው፤ ማሻሻያውን ለመተግበር ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በማርታ ጌታቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.