በአማካይ በቀን እስከ 10 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ይጓጓዛል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀን እስከ 10 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እያጓጓዘ መሆኑን የማሪታይም እና ትራንዚት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የአገልግሎቱ ሥራ አስኪያጅ ሙስጠፋ ገለቶ እንዳሉት፤ ባቡር እና ሌሎች ማጓጓዣዎችን በመጠቀም ወደብ ላይ ያሉ ዕቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡
ዘንድሮ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በአማካይ በቀን እስከ 10 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ እያጓጓዝን ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የጅቡቲ ዩኒ ሞዳል ኃላፊ ሲራክ መንበሩ በበኩላቸው፤ የአፈር ማዳበሪያን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የኦፕሬሽን ኮሚቴ ተቋቁሞ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመልቲ ሞዳል ዲፓርትመንት ምርቶች ጅቡቲ ወደብ ከደረሱ በኋላ ተገቢውን ሂደት አልፈው ወደ ሀገር እንዲገቡ እየሠራን ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የጅቡቲ መልቲ ሞዳል ኃላፊ ብርሃን ተሾመ ናቸው።
በኢትዮጵያ ወደ ሚገኙ ደረቅ ወደቦች ብሎም እስከ ግል መጋዘን በማጓጓዝ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡም ነው ያስታወቁት፡፡
በዮናስ ጌትነት