Fana: At a Speed of Life!

 ሀገራችን በተለያየ ጊዜ የተደገሰላትን የጥፋት ድግስ የቀለበሰ ጀግና ሠራዊት አላት – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የተደገሰላትን የጥፋት ድግስ የቀለበሰ ጀግና የመከላከያ ሠራዊት አላት ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የምዕራብ ዕዝ የተመሰረተበት 47ኛ ዓመት በዓል ‘የጽናት ተምሳሌት፤ የኢትዮጵያ ጋሻ’ በሚል መሪ ሀሳብ በኦሮሚያ ክልል በነቀምቴ ከተማ ወለጋ ስታዲየም እየተከበረ ነው።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባስተላለፉት መልዕክት፤ 47ኛ ዓመት ምስረታውን የሚያከብረው የምዕራብ ዕዝ ባለድል በመሆን የተቋማችን ኩሩ ዕዝ ነው ብለዋል።

ምዕራብ ዕዝ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ሊጠናቀቅ ባለበት በአሁኑ ወቅት የምስረታ በዓሉን ማክበሩ ቀኑን ልዩ እንደሚያደርገው አብራርተዋል፡፡

የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌ/ጀ መሰለ መሰረት በበኩላቸው ታሪክ እንደሚያወሳው የዕዙ ገድል ከተመሰረተበት 1970 ጀምሮ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የተሰጠውን ግዳጅ በትጋትና በፅናት የተወጣ መሆኑን አስታውሰዋል።

የሀገራችንን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ የኢትዮጵያ አለኝታነቱን ያስመሰከረ ዕዝ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጀግናው የምዕራብ ዕዝ ከፍ ያለ መስዋዕትነት በመክፈል የጠላት ስጋት የወገን መከታ ለሀገርም ጋሻ በመሆን ብዙ ጀብድ ፈጽሟል ብለዋል።

47ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ስናከብር ምን ጊዜም ዕዙ ኩራታችን መሆኑን በማሰብ ነው በማለት ተናግረዋል።

በዳባ  ፍቃዱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.