Fana: At a Speed of Life!

ኢንስቲትዩቱ ከ80 በላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን አከናወነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል የሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት አዳዲስ ፖሊሲዎችን ለማርቀቅና ለሕግ ማሻሻያ ግብዓት የሚሆኑ ከ80 በላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ማከናወኑን ገለጸ፡፡

ኢንስቲትዩቱ በተቋቋመበት ዓላማ መሠረት ለፍትሕ ተቋማት የአቅም ግንባታ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ምትኩ ማዳ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ የፍትኽ ዘርፍ የመረጃ ማዕከል በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የጥናትና ምርምር ግኝቶች በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለሚመለከታቸው አካላት እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት ተቋሙ እስከ አሁን ከ80 በላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ለሕግ ማሻሻያና ለፖሊስ ግብዓትነት እንዲውሉ ለተቋማት ማስረከቡን አረጋግጠዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም የዳኝነት ፖሊሲን ጨምሮ አምስት የጥናትና ምርምር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢንስቲትዩቱ ጥናት የሚያደርግባቸውን የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች በዋናነት ከተለያዩ ተቋማት ጥቆማዎችን በመቀበልና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የቅድመ ዳሰሳ በማከናወን እንደሚመርጥ አስረድተዋል።

ተቋሙ ለሕግ ማሻሻያ፣ ለፖሊሲና ለተለያዩ ደንቦች ግብዓት ከሚሆኑ ጥናትና ምርምሮች ባሻገር ዜጎች በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያላቸውን አተያይ በተመለከተ የእርካታ ዳሰሳ ጥናት ማከናወኑንም አንስተዋል።

ለአብነትም በቅርቡ ሂል ከተሰኘ የኔዘርላንድስ ተቋም ጋር በተከናወነው የፍትሕ አሰጣጥ የእርካታ ዳሰሳ ጥና የተገኙ ውጤቶችን መነሻ በማድረግ የመሠረተ ማህበረሰብ የፍትሕ አገልግሎት እየተተገበረ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.