የደም ባንኮችን ተደራሽነት ለማስፋት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አዳዲስ የደም ባንኮችን በመክፈት የደም ለጋሾችን ተሣትፎ ለመጨመር ያለመ የተደራሽነት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ደምና ኅብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ገለጸ፡፡
በደም ባንክ ተደራሽነት ላይ በጥናት እየታየ ብዙ መሠራት እንዳለበት የጠቆሙት የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሐብታሙ ታዬ፤ በተያዘው የበጀት ዓመት በሦስት ክልሎች በራስ አቅም 10 የደም ባንኮችን ለመገንባት ታቅዶ ሥድስቱን ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚሁ መሠረት የአሮሚያ ክልል አራት የደም ባንኮችን ለመገንባት አቅዶ የደምቢ ዶሎና የሻምቡ የደም ባንኮችን ለአገልግሎት ማብቃቱን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የሶማሌ ክልል የደም ባንኮችን ቁጥር ወደ 12 ለማድረስ አቅዶ እየሠራ መሆኑን እና በዚህም መሠረት ፊልቱ፣ ቀብሪደሃር እና ገርቦ የደም ባንኮችን ለአገልግሎት ማብቃቱን አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም አፋር ክልል የአብአላ ደም ባንክን በመገንባት በክልሉ የሚገኙ የደም ባንኮችን ቁጥር ሦስት ማድረስ ችሏል ብለዋል፡፡
የእነዚህ የደም ባንኮች ግንባታ በሀገሪቱ የሚገኙ የደም ባንኮችን ቁጥር 59 አድርሶታል ያሉት አቶ ሐብታሙ፤ ይህም በጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች በአቅራቢያቸው ደም በመለገስ በደም እጦት ሊያልፍ የሚችልን የሰው ሕይወት ለመታደግ ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በበጀት ዓመቱ 10 ወራት በሁሉም ደም ባንኮች 339 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰቡን አሳውቀው፤ የደም ሕክምና ተጠቃሚዎች ፍላጎት እና አቅርቦት አሁንም ስላልተመጣጠነ ማሕበረሰቡ ደም በመለገስ ሕይወት የማዳን ሥራን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው