በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሲዳማነት የተጠቃ መሬትን የማከም ሥራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬት በማከም የአፈር ለምነትን ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ምክትልና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አንደኛ ሽናሌ÷ በክልሉ ከሚታረሰው ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት 328 ሺህ ሄክታር መሬት በአሲዳማነት መጠቃቱን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
ይህም ከሚታረሰው መሬት የ28 በመቶ ድርሻ እንዳለውና በምርትና ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተናግረዋል።
የአፈሩ አሲዳማነት የምርቱን መጠን ከ50 በመቶ በላይ የመቀነስ ዕድል ስላለው ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬት አርሶ አደሮችን በማቀናጀት በኖራ፣ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ማዳበሪያ የማከም ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው÷ በተሰራው ሥራም ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት ከምርምር ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአፈር አሲዳማነት ችግር ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል ዘላቂ የአፈር ለምነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅም ኃላፊው አስገንዝበዋል።
በአድማሱ አራጋው