የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት 46 ዊልቼሮችን ለአካል ጉዳተኞች አበረከተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኖሩ የአካል ጉዳት ለገጠማቸው ልጆችና ለጉዳት ለተጋለጡ አዋቂዎች 46 ዊልቼሮችን አበርክቷል።
ድጋፉ የአካል ጉዳት ገጥሟቸው ከቤት ወጥተው ለመንቀሳቀስም ሆነ ወደ ትምህርት ገበታ ለመቀላቀል ችግር ለገጠማቸው ልጆችና በተለያየ ምክንያት ለጉዳት ለተጋለጡ አዋቂዎች የተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ጸሕፈት ቤቱ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድጉን እንደሚቀጥል ገልጾ÷ ድጋፉን ሲያደርግ በልጆቻቸው የአካል ጉዳት ምክንያት መስራትም ሆነ ልጆቻቸውን ማንቀሳቀስ ለተቸገሩ ወላጆች እፎይታን እንደሚያገኙ በማሰብ ነው ብሏል።
በቅርቡ የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ከቻይና የገጠር ልማት ፋውንዴሽን ጋር በጋራ በመሆን ያስመጣቸውን ዊልቼሮችን ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አዲስ አበባ ከተማ ለሚኖሩ አካል ጉዳተኞች በስጦታ በመለገስ በቀጣይ ወራት በተለያዩ የክልል ከተሞች ለአካል ጉዳተኞች የሚያደርጉትን የዊልቼር ድጋፍ ፕሮግራም ማስጀመሩ ይታወሳል።
በፍሬህይወት ሰፊው