የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ሪፎርሙ ፖሊስ ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ አስችሎታል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ሪፎርም ፖሊስ ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ አስችሎታል ብለዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማት በርካታ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውንና የፌደራል ፖሊስም ተልዕኮውን በብቃት መወጣት የሚያስችል ለውጥ ማድረጉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሀገር ሰላምና ጸጥታ በውጤታማነት እንዲጠበቅ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ አሁን ላይ በብቁ የሰው ኃይል፣ በትጥቅ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የላቀ ቁመና መፍጠሩን አስረድተዋል።
ይህም ኮሚሽኑ የወንጀል መከላከልና መመርመር ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣና የህዝብን ሰላምና ጸጥታ ይበልጥ እንዲያረጋግጥ ማስቻሉን ተናግረዋል።
ፖሊስ በጀግንነት መጠበቅ፤ በሰብዓዊነት ማገልገል በሚለው መርህ ከ600 በላይ ተቋማትና መሰረተ ልማቶችን በጀግንነት በመጠበቅ ደኅንነታቸውን እያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በሀገራዊ የሰላምና ጸጥታ ስራዎች በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በሸኔ የሽብር ቡድንና በጽንፈኛው ቡድን ላይ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ህግ የማስከበር እርምጃ በመውሰድ ትርጉም ያለው ስራ መሥራቱን ተናግረዋል።
በዚህም በአብዛኛው አካባቢዎች የተሻለ ሰላምና ጸጥታ መኖሩን ጠቅሰው፥ የታጠቁ አካላትም በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን እየሰጡና የተሃድሶ ስልጠና በመውሰድ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሀገር ላይ የተቃጡ የሽብር እቅዶችን አስቀድሞ ማክሸፍ መቻሉን ጠቅሰው÷ ከዚሁ ጋር በተገናኘ 972 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ውሳኔ እያገኘ መሆኑንም ተናግረዋል።
በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የተሳተፉ 29 ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ መሆናቸውን አንስተው÷ በኮንትሮባንድ ቁጥጥር በዘጠኝ ወራት ብቻ ከ15 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸውን እቃዎች መቆጣጣር መቻሉን ገልጸዋል።
የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና የሀገርን ሃብት የማዳንና ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ እየተሰራ እንደሆነም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በቴክኖሎጂ የታገዘ የማጭበርበር ወንጀልን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራን በማጠናከር በኩል ከባንኮችና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውቀዋል።
በዚህ ሂደትም ከ80 በላይ ወንጀል ፈጻሚዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ከ500 በላይ የባንክ ደብተሮችን በማገድ ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ኮሚሽኑ ህብረተሰቡ የወንጀል ጥቆማዎችን የሚሰጥበት የዜጎች መተግበሪያን ስራ ላይ በማዋል ቅንጅታዊ ስራን እያጠናከረ እንደሚገኝም ኮሚሽነር ጀነራሉ ጠቁመዋል።