ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው እቃዎች የሚሸጡበት የገበያ ማዕከል በፒያሳ…
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው እቃዎች የሚሸጡበት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የገበያ ማዕከል ግንባታ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው አሉ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባ አዳነች በፒያሳ መልሶ ማልማት እየተገነባ የሚገኘውን አራዳ ሌግዤሪ የገበያ ማዕከል ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ ተመልክተዋል፡፡
ከንቲባዋ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ አዲስ አበባ በውበት፣ በጽዳት እና በአጠቃላይ ገጽታ በብዙ መንገድ እየተቀየረች ነው፡፡
አዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ተቋማት ያሉባት የዲፕሎማሲ ማዕከል ከተማ እንደሆነች አውስተዋል፡፡
ይህም ለከተዋማ ትልቅ እድል መሆኑን ጠቁመው ÷ እድሉን ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይም አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነቷን የሚያረጋግጡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት፡፡
ለአብነትም በፒያሳ እየተገነባ የሚገኘው አራዳ ሌግዤሪ ሞል ሲጠናቀቅ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸውን እቃዎች ለመግዛት ወደ ዱባይና ሌሎች ሀገራት የሚደረገውን ጉዞ ያስቀራል ብለዋል፡፡
የገበያ ማዕከሉ ሁለት ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን ÷ ሁሉንም አይነት ግብይት መፈጸም እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከመዝናኛ ሥፍራዎች፣ ከመኪና ማቆሚያ ማዕከላት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ጋር ተሰናስሎ እየተገነባ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የገበያ ማዕከሉን በጥራትን በፍጥነት አጠናቅቆ ወደ ሥራ ለማስገባት በቅንጅትና በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ