በብሪክስ ጉባኤ ለአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት በመስጠት ውይይት ተደርጓል – ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በብሪክስ ጉባኤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት አስፈላጊ ስለመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል አጽንኦት ተሰጥቶታል አሉ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በብራዚል የብሪክስ 17ኛ ጉባዔ ላይ የነበረውን ቆይታ አስመልክቶ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ጫና በማሳደሩ የዓለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ መሆኑ በጉባኤው ተነስቷል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የደን እና አካባቢ ጥበቃ ሥራን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት በከፍተኛ ደረጃ እየሰራችበት እንደሆነ በመግለጽ፤ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቁርጠኛ በመሆን ተግባሩን በፋይናንስ እንዲደግፍ ተጠይቋል ነው ያሉት፡፡
በካይ ጋዞችን በመልቀቅ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ያደጉ ሀገራት የላቀ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው በጉባኤው የተሳተፉ መሪዎች ስለመስማማታቸው አንስተዋል።
የብሪክስ አባል ሀገራት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው መወያየታቸው ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የብሪክስ አባላት የቴክኖሎጂና የፋይናንስ ትብብር እንዲያደርጉ ከስምምነት መደረሱን የገለጹት ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በዚህ ሂደት ተጠቃሚ ትሆናለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታዳሽ የሃይል ምንጭ ላይ ከፍተኛ ስራ እየሰራቸው እንደሆነ አንስተው፤ ከሀገር አልፎ ለሌሎች የሚተርፈውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለማስወግድና የታዳሽ የሃይል ምንጭን ለማሳደግ የሚያደረገውን ጥረት ያግዛል።
የኢትዮጵያ የሃይል አማራጭ ግንባታ የአየር ንብረት ለውጥ ጫና ተጋላጭነትን የሚቀንስ በመሆኑ የኢንቨስትመንት እድሎችን በመሳብም ተጠቃሚ መሆን እንደሚያስችላት አብራርተዋል፡፡
በኮሪደር ልማት የተሰራው ስራ ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲሁም ለአገልግሎት አሰጣጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የትራፊክ መጨናነቅን በመቀነስ እና ሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም የነዳጅ አጠቃቀምን በማሻሻል የአየር ብክለትን ለመቀነስ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አሻራ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት በተጨባጭ እየሰራች ስለመሆኗ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በአቤል ንዋይ