እየተከናወኑ ያሉ ሀገራዊ ግንባታዎች ለዘላቂ ብልጽግና አስተማማኝ መሰረቶች ናቸው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመደመር እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ ሀገራዊ ግንባታዎች ለዘላቂ የኢትዮጵያ ብልጽግና አስተማማኝ መሰረቶች ናቸው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት ኢትዮጵያ ትገነባለች፤ ፈጠራ፣ ፍጥነትና ጥራት ለመሰረተ ልማት እመርታ በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ በተጀመረው የኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሳምንት እንዲሁም አውደ ርዕይ ባስጀመሩበት ወቅት ነው።
በዚሁም ባለፉት የለውጥ ዓመታት በመሠረተ ልማት ረገድ ያሳየነው ቆራጥነት ለብዙዎች ተዓምር ቢመስልም ለእኛ ግን የዕለት ተዕለት ተግባራችን ነው ያሉት።
በተለይም በመንገድ፣ በኃይል፣ በዲጂታል ምህዳር፣ በመስኖ፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታና ማስፋፊያ እንዲሁም በከተማ ልማት ያስመዘገብናቸው ስኬቶች ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እየዘረጋች ያለችው መሠረት ምን ያህል የጸናና ጥልቅ እየሆነ እንደሚገኝ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብልፅግና በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆም እና ለማሳለጥ መሰረተ ልማትን በልዩ ትኩረት እየመራንና እያጠናከርን እንገኛለን ሲሉም አብራርተዋል።
መሰረተ ልማት ለእኛ የደም ስራችን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ እንዲሁም ሌሎች የክልልና የዞን ከተሞች የኮሪደር ልማት ከተባበርንና ተግተን ከሰራን የማይቻል የለም የሚለውን መርህ በተግባር ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል፡፡
ፍጥነትና ጥራት እንዴት ተባብረው ውጤት እንደሚያመጡ ትምህርት የተወሰደበትና ተሞክሮ የተቀመረባቸው ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በዲጂታል ዘርፍ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በማሳካት የሞባይል ተጠቃሚዎችን ቁጥር ወደ 97 ሚሊየን እንዲሁም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ወደ 57 ሚሊየን ማሳደግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
ዛሬ ላይ 28 ከተሞች የ5ጂ እና 1 ሺ 70 ከተሞች የ4ጂ ኔትወርክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን በማጽደቅ የተሟላ ትግበራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሀገርን መገንባት እንጂ እያፈረሱ ከዜሮ መጀመር እንደማይመጥነን በተግባር እያሳየን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን÷ ትናንት የተገነባው ለዛሬ፣ ዛሬ የምንገነባው ደግሞ ለነገው ትውልድ ኩራት ነው ብለዋል።
በለይኩን ዓለም