በኦሮሚያ ክልል 4 ነጥብ 67 ቢሊየን ሊትር ወተት ተመረተ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2017 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 67 ቢሊየን ሊትር ወተት ተመርቷል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ ጎሞሮ ደሬሳ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የሌማት ትሩፋት በክልሉ የወተት ምርትን ከማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
በመርሐ ግብሩ ለወተት ምርት የተሻሻሉ የላም ዝርያዎችን ለማቅረብ መሰራቱን ጠቁመው ÷ 2 ነጥብ 58 ሚሊየን በላይ የተዳቀሉ የወተት ላሞችና ጊደሮች መሰራጨታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም 828 ሺህ 330 ጥጃዎች ተወልደዋል ያሉት ዳይሬክተሩ÷ በቀጣይ በዘርፉ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱም 3 ነጥብ 571 ቢሊየን ወተት ለማምረት ታቅዶ 4 ነጥብ 67 ቢሊየን ሊትር ወተት ማምረት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የሚመረተው የወተት ምርት በአግባቡ ለገበያ እንዲቀርብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ