በአዲስ አበባ የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው አለ የከተማ አስተዳደሩ መንገዶች ባለስልጣን፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሙዲን ረሻድ (ኢ/ር) ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በአዲስ አበባ ከኮሪደር ልማቱ ጋር በማሰናሰል በርካታ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከሰሞኑ በመዲናዋ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ከተከሰተው ጎርፍ ጋር በተያያዘ አንዳንዶች ያልተገባና ትክክል ያልሆነ አስተያየት ሲያሰራጩ ተስተውሏልብለዋል፡፡
ሰሞኑን በመዲናዋ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች የመንገድ መዘጋት መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የቱቦዎችና “ማን ሆሎች” በደረቅ ቆሻሻ፣ ጣውላ እና ሌሎች ቁሶች የመደፈን ሁኔታ መከሰቱን ነው ያብራሩት፡፡
በዚህ ሳቢያም በመዲናዋ አንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍ አስፓልት ላይ የመቆየት ሁኔታ መስተዋሉን አስገንዝበዋል፡፡
በሌላ በኩል ጊዮን አካባቢ እየተሰራ ካለው የወንዝ ዳርቻ ልማት ጋር በተያያዘ ጊዜያዊ የውሃ ማቆያ ግድብ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎም ጎርፉ ግድቡን ጥሶ መውጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
ጎርፍ ተፈጥሯዊ ክስተት በመሆኑ መሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ማዋል አዳጋች ስለመሆኑ በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገራት ጭምር እየተፈተኑ ያሉበት ሁኔታ ተጨባጭ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ነው ያሉት፡፡
በኮሪደር ልማቱ መሰል ችግሮችን ለመከላከል በርካት ሥራዎች መከናወናቸው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ÷ በዚህም ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች በተገቢ ሁኔታ መታደስና መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ የተስተዋለው ክስተት ቅጽበታዊ መሆኑን አንስተው÷ የነዋሪዎች የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ሥርዓት ለችግሩ መፈጠር ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል በቅርበት እየተሰራ ነው፤ ከክስተቱ ጋር በተያያዘም የግንዛቤ እጥረት መኖሩን አስገንዝበዋል፡፡
ከባድ ዝናብ መጣልን ተከትሎ ከላይ በጠቀሱ ችግሮቸ ሳቢያ ጎርፍ ከ10 እስከ 15 ደቂቃ አስፓልት ላይ ሊቆይ እንደሚችል አንስተው÷በአጭር ጊዜ ግን በተዘረጋው ፍሳሽ ማስወገጃ መስመር እንደሚስተናገድ አብራርተዋል፡፡
ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ አንጻርም የሚጥለው ዝናብ መጠን ከፍተኛ ከሆነ የጎርፍ መጥለቅለቅና መሰል ችግሮች በአደጉ ሀገራት ከተሞችም ጭምር እንደሚከሰቱ ጠቁመዋል፡፡
በመዲናዋ መሰል የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ