በሱሉልታ ክፍለ ከተማ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል …
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሸገር ከተማ አስተዳደር ሱሉልታ ክፍለ ከተማ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው ፡፡
በሱሉልታ ክፍለ ከተማ በዛሬው ዕለት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋዎች ተከስተው እንደነበር የከተማው ነዋሪዎች ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በክረምት ወቅት በተደጋጋሚ የሚከሰተው ጎርፍ ከፍተኛ ስጋት እንደሆነባቸው ጠቁመው÷ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ አለመተግበሩ እንዳሳሰባቸውም አመልክተዋል።
በዛሬው እለት በከተማው የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከተሎ የተከሰተው ጎርፍ በተቋማት ፣ መኖሪያ ቤት እና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቅሰዋል።
ክረምቱ እየጠነከረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ÷ የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የሱሉልታ ከተማ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ወዚራ ጀማል በበኩላቸው÷ የከተማው የመሬት አቀማመጥ ለጎርፍ ተጋላጭ በመሆኑ ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል ሲሰራ ቢቆይም ከአቅም በላይ በመሆኑ በተወሰኑ አካባቢዎች ጉዳት ማድረሱን አንስተዋል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጥናት መካሄዱን የተናገሩት ምክትል ዋና አስተዳዳሪዋ ÷ በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
በተለይም በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት የጎርፍ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሆን ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡