ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በውጤታማነቱ ዓመታትን የተሻገረ ተቋም ነው – የትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደ ሌሎች አንጋፋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተወዳዳሪነት ብቻ ሳይሆን በውጤታማነትም ዓመታትን የተሻገረ ነው አሉ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያ ሆስፒታል 100ኛ እና የዩኒቨርሲቲው 70ኛ ዓመት የማጠቃለያ መርሐ ግብር አካል የሆነው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።
ጉባኤው ዩኒቨርሲቲዎች ሃሳቦቻቸውንና ስራዎቻቸውን አቅርበው ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ መሆኑም ተገልጿል።
በመድረኩ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ እንዳሉት÷ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደ ሌሎች የሀገሪቱ አንጋፋ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተወዳዳሪነት ብቻ ሳይሆን በውጤታማነትም ዓመታትን የተሻገረ ነው።
ተቋሙ እስካሁን ያከናወናቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ተግባራትን በማስቀጠል ለሌሎችም ተሞክሮውን የበለጠ እንዲያጋራ ጠይቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ተቋሙ በተለያዩ ተግባራት ሲሰጥ የቆየው አገልግሎት ለዛሬ ከፍታ ማድረሱን አንስተዋል።
የተቋሙ ማስተማሪያ ሆስፒታል በህክምናው ዘርፍ ዘመኑ የደረሰበትን አገልግሎት እስከመስጠት መድረሱን ገልጸው÷ ዩኒቨርሲቲውም ባከናወናቸው የምርምር ተግባራት በርካታ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ሽልማቶች ማግኘቱን አስታውሰዋል።
በሙሉጌታ ደሴ