የቀደሙ ችግሮቻችንን በይቅርታ በመፍታት ለሀገራችን መፍትሄ ማምጣት አለብን – መምህር ዘበነ ለማ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀደሙ ችግሮቻችንን በይቅርታ በመፍታት ለሀገራችን መፍትሄ ማምጣት አለብን አሉ መምህር ዘበነ ለማ (ዶ/ር)።
መምህር ዘበነ ለማ (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ኢትዮጵያውያን በሁሉም አካባቢ የየራሳቸው የሽምግልና ስርዓትና ሌሎች መልካም እሴቶች እንዳሏቸው አንስተዋል፡፡
እነዚህን እሴቶች ተጠቅመን ሊከፋፍሉን የሚችሉ ነገሮችን ወደ መልካም መለወጥ መቻል አለብን ብለዋል፡፡
ዛሬም የቀደመውን እያነሳን በትናንት መንገድ መሄድ ሳይሆን በይቅርታ ቋጭተን ለሀገራችን መፍትሄ ለማምጣት ልቦናችን ለይቅርታ የተዘጋጀ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
ካለንበት ችግር የምንወጣው ሰፊ ልብ ሲኖረን ነው ያሉ ሲሆን፥ ሁሉም ሰው በየተሰማራበት ሙያ በታማኝነት ማገልገል ከቻለ ሀገር ሰላም እንደምትሆን አስረድተዋል፡፡
ሀገር የሚገነባው ቤተሰብ ሲገነባ መሆኑን ገልጸው፥ እንደ ማህበረሰብ ሰላም ለመፍጠር የእያንዳንዱን ቤተሰብ ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ ረገድ የሀይማኖት ተቋማት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
መምህር ዘበነ ለማ (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር የነበራቸውን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ፡ https://www.youtube.com/watch?v=7duGQ3-3GHw
በብርሃኑ አበራ