በሜዳ ውስጥ ውዝግቦች መሃል የማይታጣው ኮከብ ዲያጎ ኮስታ…
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በስታምፎርድ ብሪጅ የሚወደድ እና በሜዳ ላይ በሚኖሩ ውዝግቦች መሃል የማይጠፋ ኮከብ ነው የቼልሲ የቀድሞ ተጫዋች ዲያጎ ኮስታ፡፡
በአስፈሪ ቁጣው የሚታወቀው ዲያጎ ኮስታ ሜዳ ላይ ከሚያሳየው ድንቅ ብቃት በተጨማሪ በሃይለኛነቱ እና ሜዳ ላይ በሚኖሩ አለመግባባቶች ውስጥ ግንባር ቀደም መሆኑ ይታወሳል፡፡
ዲያጎ ኮስታ በእግር ኳሱ ዓለም ራሱን ከኮከቦች ተርታ ለማሰለፍ ያገኛቸውን ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀም ራሱን ከፍ አድርጎ ማሳየት የቻለ ሲሆን÷ ባደረገው ጥረትና ታታሪነቱም ራሱን ወደ ድንቅ አጥቂነት መቀየር ችሏል፡፡
ዲያጎ ኮስታ ለቼልሲ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ወልቭስ፣ ቦታፋጎ፣ ግሬሚዮ፣ አትሌቲኮ ሚኔሮ፣ ሪያል ቫላዶሊድ እና ብራጋን ለመሳሳሉ ክለቦች ተጫውቷል፡፡
ኮስታ በስፔኑ ክለብ አትሌቲኮ ማድሪድ በነበረው ቆይታ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ከመሆን ባለፈ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር የስፔን ላሊጋ ዋንጫን ማንሳቱ አይዘነጋም፤በተጨማሪም በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር እስከ ፍጻሜ ድረስ መጓዝ ችሏል፡፡
ዲያጎ ኮስታ በፈረንጆቹ 2014/15 የውድድር ዓመት ቼልሲ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ሲያሳካ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ፤ በቼልሲ ቤት በፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ ስር ተመራጭ አጥቂ እንደነበረም አይዘነጋም፡፡
በምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ በመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ ድንቅ ጊዜን ማሳለፍ የቻለው ኮስታ በሊጉ ባደረጋቸው 26 ጨዋታዎች 20 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
በቼልሲ በቆየባቸው ዓመታት ውዝግብ እና ግጭት ውስጥ የማይጠፋው ኮስታ ግብ የሚያስቆጥርበት መንገድ እና ብቃቱ ድንቅ ነበር፡፡
ከተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች ጋር በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ሲገባ የሚስተዋለው ዲያጎ ኮስታ የቼልሲ ወሳኝ ተጫዋች ከመሆን ግን ያገደው ነገር አልነበረም፡፡
ከጆዜ ሞሪኒሆ ስንብት በኋላ ኮስታ በአንቶኒዮ ኮንቴ ስር በፈረንጆቹ 2016/2017 የውድድር ዓመት በሊጉ ባደረጋቸው 35 ጨዋታዎች 20 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን÷ በ3 ዓመታት ውስጥ 2ኛ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫንም ማሳካት ችሏል፡፡
በወቅቱ ኮስታ በሜዳ ላይ የሚያሳየው እንቅስቃሴው ጥሩ ቢሆንም ከአሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ ጋር ግን አለመግባባቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ኮስታ በክለቡ ተጨማሪ ዋንጫን ቢያሳካም በሁለቱ አለመግባባት እና አንቶኒዮ ኮንቴ በእሳቸው ዕቅድ ውስጥ እሱ እንደሌለ ለራሱ መናገራቸውን ተከትሎ ከቼልሲ ጋር ሊለያይ ግድ ብሎታል፡፡
ኮንቴ እንደማይፈልጉት ነግረውት ቼልሲን በዚህ መንገድ ቢለቅም ዲያጎ ኮስታ ግን በቼልሲ ቆይታው በሰራቸው ሥራዎች በደጋፊዎቹ የሚረሳ ተጫዋች አይደለም፡፡
ዲያጎ ኮስታ ከብራዚሉ ክለብ ግሪሚዮ ከተለያየ በኋላ ከፈረንጆቹ ጥር 31 ቀን 2025 ጀምሮ ነጻ ወኪል ተጫዋች ሆኖ ይገኛል፡፡
በሜዳ ላይ በሚኖሩ ውዝግቦች እና ግጭቶች መሃል የማይጠፋው የቼልሲ ተወዳጅ ተጫዋች ዲያጎ ኮስታ ልክ በዛሬዋ ዕለት ነበር በፈረንጆቹ 1988 የተወለደው፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ