ኢትዮጵያ ላይ እየጨመረ የመጣውን የሳይበር ጥቃት የመመከት አቅም…
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ አየጨመረ መጥቷል አሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ “የሳይበር ደኅንነት የዲጂታል ኢትዮጵያ መሠረት” በሚል መሪ ሐሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ22ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ6ኛ ጊዜ የሳይበር ደህንነት ወር ከጥቅምት 1 እስከ ጥቅምት 30/2018 ይከበራል፡፡
የሳይበር ደህንነት ወርን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሯ÷ ኢትዮጵያ ላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መበራከቱን ጠቁመዋል፡፡
ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚሞከሩ የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል ወሳኝ መሆኑን አንስተው÷ በተለይም እንደ ሀገር የዲጂታላይዜሽን መስፋፋትን ተከትሎ የሳይበር ጥቃቶቹ በ2017 ዓ.ም ወደ 13 ሺሕ 496 ከፍ ማለቱንና መመከት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ መልኮች የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መጨመሩንና በተለይም የመሠረተ ልማት አገልግሎት የማቋረጥ፣ የገጸድር ጥቃት፣ የተቋማት እና ሌሎች አገልግሎቶችን የማቋረጥ ሙከራዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።
ሁሉም ዜጋ ራሱን ከጥቃት የመከላከል ስራ በንቃት መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
6ኛው የሳይበር ደህንነት ወር በሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ አንስተው÷ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ያለመ ንቅናቄ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የዲጂታላይዜሽን ደኅንነት በዲጂታላይዜሽን ጉዞ የተቋማትን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችል ንቅናቄ በመርሐ ግብሩ እንደሚከናወን አመላክተዋል።
በግዛቸው ግርማዬ