አርሰናል ከአትሌቲኮ ማድሪድ እና ሌሎች የዛሬ ጨዋታዎች…
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የሦስተኛ ዙር መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት ዘጠኝ ጨዋታዎች በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ይደረጋሉ፡፡
በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ምሽት 1 ሰዓት ከ45 ባርሴሎና የግሪኩን ኦሎምፒያኮስ በሜዳው ሲያስተናግድ፥ የካዛኪስታኑ ካይራት አልማቲ ከቆጵሮሱ ፓፎስ ጋር ይጫወታሉ፡፡
ምሽት 4 ሰዓት ላይ አርሰናል በሜዳው ኤሚሬትስ የስፔኑን ክለብ አትሌቲኮ ማድሪድ የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም እርስ በእርስ የተገናኙት በ2017/18 በዩሮፓ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ ሲሆን፥ አትሌቲኮ ማድሪድ በደርሶ መልስ ውጤት 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ ማለፉ ይታወሳል፡፡
ከስፔን ክለቦች ጋር ያደረጓቸውን ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት መድፈኞቹ የዛሬውን ጨዋታ የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በተመሳሳይ 4 ሰዓት የአምናው የመድረኩ ሻምፒዮን ፒኤስጂ ከሜዳው ውጭ ባየር ሊቨርኩሰንን የሚገጥም ሲሆን፥ የፍጻሜው ተፋላሚ ኢንተር ሚላን ከሜዳው ውጭ ከቤልጂየሙ ኡኒየን ሴን ጂሎዝ ጋር ይገናኛል፡፡
ቪያሪያል ከማንቼስተር ሲቲ፣ ፒኤስቪ አይንድሆቨን ከናፖሊ፣ ኒውካስል ዩናይትድ ከቤኔፊካ እንዲሁም ኤፍሲ ኮፐንሀገን ከቦሩሺያ ዶርቱመንድ በተመሳሳይ ምሽት 4 ሰዓት የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡