ፈረንሣይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር ይበልጥ ታጠናክራለች – ጄ/ል ፒየር ሺል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፈረንሣይ ከኢትዮጵያ ጋር በወታደራዊ መስክ ያላትን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ዝግጁ ናት አሉ የሀገሪቱ ምድር ጦር አዛዥ ጄኔራል ፒየር ሺል።
በጄነራል ፒየር ሺል የተመራ የፈረንሣይ ወታደራዊ ልዑክ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር ተወያይቷል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመው ምክክሩ በቀጣይ በሚኖሩ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተመላክቷል፡፡
ወታደራዊ ትብብሩ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ያደረጓቸውን ስምምነቶች ተከትሎ የተደረገ መሆኑን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
ጄኔራል ፒየር ሺል በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሠላም ለማረጋገጥ እየሠራች ባለው ሥራ መደሰታቸውን ገልጸው÷ በቀጣይነት አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በሠላም ማስከበር ተልዕኮ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተሣትፎ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት አዛዡ ÷ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ፈረንሳይ ለጋራ ተጠቃሚነት በወታደራዊ ቁሳቁስ ድጋፍ፣ በሠው ኃይል ሥልጠና እና ያልተቆራረጠ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
የመከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን በበኩላቸው ÷ ዘመኑ በሚጠይቀው ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ ግዳጅ ለመወጣት ከፈረንሣይ ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
ከፈረንሣይ ጋር የረጅም ዓመታት ወታደራዊ ግንኙነት መኖሩን አስታውሰው ÷ ይህን የቆየ ወዳጅነት በተለያዩ ወታደራዊ ዘርፎች አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት፡፡