ታፍራና ተከብራ የምትጸና ኢትዮጵያን ለመገንባት አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ታፍራና ተከብራ የምትጸና ኢትዮጵያን ለመገንባት አንድነታችንን ይበልጥ ማጠናከር አስፈላጊ ነው አሉ።
የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ በፋሲለደስ ባሕረ ጥምቀት በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
በአከባባር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተገኝተዋል።
እንዲሁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማሕበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ በአከባበር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ፥ የበዓሉን ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴት ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ መስራት ይገባል።
የኢትዮጵያዊነት መገለጫው አብሮነት፣ መተሳሰብና መረዳዳት መሆኑን አውስተው፥ ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተዋይ ትዕግስተኛና ጀግና እንዲሁም አርቆ አስተዋይ እንደሆነ አውስተዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የመንግሥትን ዋጋና ፋይዳ በቅጡ ይረዳል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ያሉንን እድሎችና ተስፋዎች በተገቢ ሁኔታ መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ተገማች ባልሆየውና ትርምስ በበዛበት ዓለም ዘመኑን የዋጀ አካሄድን መምረጥ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ውጤታማ ሆኖ ለመዝለቅ ማስተዋልና መስከን እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
ኢትዮጵያ በርካታ ጠላቶች አሏት፤ እንድናድግና እንድንበለጽግ አይፈልጉም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ይህን ለመመከትም በአንድነት መቆም ይገባል ብለዋል።
አላማችን ታፍራና ተከብራ የምትጸና ኢትዮጵያን መገንባት ነው፥ ለዚህም አንድ ሆኖ መቆም አስፈላጊ እንደሆነ አብራርተዋል።
አባቶች ያቆዩትን የኢትዮጵያ መገለጫ ሁሉ ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ሃላፊነት እንዳለበት አመልክተዋል።
አቶ አረጋ ከበደ በኩላቸው ፥ የጥምቀት በዓልን በታሪካዊቷ ጎንደር ሊታደሙ ለመጡ እንግዶች እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
የጥምቀት በዓል ከኃይማኖትና ባህላዊ እሴቱ ባለፈ በርካታ ትሩፋቶች እንዳሉት ገልጸዋል።
የአብሮነትና መተሳሰብ በዓል የሆነው ጥምቀት ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚ ፋይዳው ጉልህ እንደሆነም ተናግረዋል።
በመላኩ ገድፍ