Fana: At a Speed of Life!

በህገ ወጥ መንገድ ግለሰቦችን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ ወንጀል የተከሰሱ በእስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በህገ ወጥ መንገድ ሰባት ግለሰቦችን በጅቡቲ በኩል ወደ ውጭ ሀገር በመላክ የወንጀል ድርጊት የተከሰሱ በጽኑ እስራት እና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።

ተከሳሾች ነኢም አወል እና ሰይድ (ሳዲቅ) ሀሰን የተባሉ ደላሎች ናቸው።

በፍትህ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ማስተባበሪያ ዐቃቤ ሕግ በ2017 ዓ.ም በተከሳሾቹ ላይ በሰው የመንገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ 8 ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተደነገገውን ድንጋጌን መተላለፋቸውን ጠቅሶ በተለያዩ መዝገቦች ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በአንደኛው ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው፤ 1ኛ ተከሳሽ አራት የግል ተበዳዮችን በተለያየ ጊዜ ‘ሳዑዲ አረቢያ እልካችኋለው’ በማለት ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን ግራዋ ወረዳ ወደ ድሬዳዋ አምጥቷል።

ከዚህ በኋላም ተከሳሹ ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ጫካ በማሳደርና በእግርና በተሽከርካሪ ወደ ጅቡቲ ድንበር በመውሰድ የግል ተበዳዮች ቤተሰቦች ጋር ስልክ በመደወልና በስልክ የግል ተበዳዮችን እያሰቃዩና እየደበደቡ ስቃያቸውን እንዲሰሙ በማድረግ ገንዘብ ካልከፈሉ እንደሚገሏቸው ሲያስፈራሯቸው እንደነበር በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

በዚህ መልኩ ከ3 የግል ተበዳይ ቤተሰቦች በባንክ ሂሳቡ በተለያየ መጠን ገንዘብ እንዲገባ ካደረገ በኋላ ጅቡቲ ሲደርሱ የግል ተበዳዮችን ጥለዋቸው የተሰወሩ መሆኑ በክሱ ተመላክቷል።

በተጨማሪም አራተኛ የግል ተበዳይ የሆነውን ረመዳን እንዋር መሀመድ የተባለ ግለሰብን ደግሞ ወደ ወላጅ እናት ጋር ስልክ መደወል “ብር ላኪ አለበለዚያ ልጅሽን እገለዋለው” በማለት ከዛቱ በኋላ በሁለተኛው ቀን የተከሳሽ ግብረአበር የግል ተበዳይን በዱላ ጭንቅላቱን በመምታች ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገ መሆኑ በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

በሌላኛው የክስ መዝገብ የተከሰሰው ሰይድ (ሳዲቅ) ሀሰን የተባለ ተከሳሽ ላይ በቀረበ ዝርዝር ክስ እንደተመላከተው፤ ተከሳሹ ሶስት የግል ተበዳዮችን በተለያየ ጊዜ ከሚኖሩበት ኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ‘የመን እወስዳችኋለው’ በማለት በማስማማት በመኪና እና በእግር በማጓጓዝ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ድንበር በማድረስ ላልተያዘ ግብረአበሩ አስረክቧል።

ተከሳሹ ለተበዳይ ቤተሰቦች ስልክ በመደወል ገንዘብ ካላስገቡ እንደሚገሏቸው በማስፈራራት እና ተበዳዮችን በመደብደብ የሲቃይ ድምጽ በስልክ ለቤተሰቦቻቸው ሲያሰሙ እንደነበርና ገንዘቡ ከገባለት በኋላ ደግሞ ተበዳዮችን ጠረፍ ላይ ጥሏቸው መሰወሩ በክስ ዝርዝሩ ላይ ተጠቅሷል።

ተከሳሾቹን የድሬዳዋ ከተማ ፖሊስ በክትትል በቁጥጥር ስር ካዋላቸው እና የጊዜ ቀጠሮ ምርመራ ከተጣራባቸው በኋላ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ድሬዳዋ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ተከሳሾ የቀረበባቸው ክስ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ የሰው ምስክሮችንና የሰነድ ማስረጃዎችን ለችሎቱ አቅርቧል።

ችሎቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ ስር እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃ መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ ማስረጃ መርምሮ በመያዝ ነኢም አወል በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እና 200 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

እንዲሁም ሰይድ (ሳድቅ) ሀሰን በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ100 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.