ሥራና ሰራተኛ በቀላሉ የሚገናኝበት የዲጂታል ሥርዓት…
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሥራ ገበያ ምኅዳሩን በውጤታማ የዲጂታል ሥርዓት በማዘመን ሥራና ሰራተኛ በቀላሉ የሚገናኝበት ዕድል እየተፈጠረ ነው አሉ የሥራ ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር ያለማውን ሥራና ሰራተኛ በቀላሉ የሚገናኝበት ‘ፈልጉልኝ’ የተሰኘ ዘመናዊ የዲጂታል መተግበሪያ ይፋ አድርጓል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ የዜጎችን የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያዘምኑ የዲጂታል አማራጭ የማሻሻያ ርምጃዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።
አዲሱ መተግበሪያ ሥራና ሰራተኛን በቀላሉ የሚያገናኝ የዲጂታል አማራጭ መሆኑን ገልጸው÷ በሁሉም ዘርፍ ሙያና ክህሎት ያላቸውን ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት የሚያሰፋ እንደሆነ ተናግረዋል።
መተግበሪያውን ከፋይዳና የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ጋር በማስተሳሰር በተለያዩ የቋንቋ አማራጮች ተደራሸ የማድረግ ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።
በመተግበሪያው የተካተቱ የተሟላና አስተማማኝ የቴክኖሎጂ አማራጮች ፍትሐዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ምኅዳርን በመፍጠር የማይተካ ሚና እንዳለውም አንስተዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው÷ መተግበሪያው በሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ዕውቀት የለማና ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ብለዋል።
ይህም የመረጃ ሉዓላዊነትና ደህንነትን ለማስጠበቅ ተደማሪ አቅም እንዳለው በመግለጽ አምስት የሀገር ውሰጥ ቋንቋዎችና አጭር የስልክ መልዕክት አማራጭ በመተግበሪያው መካተታቸው የዜጎች ተጠቃሚነትን ለማላቅ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።