ለኢትዮጵያ ማከናወን የባህር በር…
የኢትዮጵያና የቀይ ባህር ታሪክ ሊነጣጠል የማይችል የህልውና ታሪክ ነው። በጥንት ዘመን የሥልጣኔና የብልጽግና ምንጭ የነበረው ይህ ባህር፣ ዛሬም ቢሆን ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና ቀጣናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወሳኝ ነው፡፡
ታሪክ የሚያስተምረን፣ የኢትዮጵያ ደህንነትና ልማት ሁልጊዜም ከቀይ ባህር ሰላምና መረጋጋት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ነው።
አሰብ ወደብ ለብዙ አሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ ዋነኛ የኢኮኖሚና የስትራቴጂካዊ መውጫ በር በመሆን አገልግሏል።
በአፄ ኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመነ መንግሥት በአሰብ ወደብ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኢንቨስትመንት ተደርጓል።
ትልቅ የነዳጅ ማጣሪያ ተገነባ፣ ከወደቡ እስከ አዲስ አበባ የሚዘልቅ የጭነት መኪና መንገድ ተዘረጋ፣ እንዲሁም ጠንካራ የባህር ኃይልና የንግድ መርከብ ድርጅቶች ተቋቋሙ።
ወደቡም ዋነኛ የኢትዮጵያ መውጫ መግቢያ በር ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ክስተት ኢትዮጵያን ከዚህ ወሳኝ ወደብ እንድትገለልና ሙሉ በሙሉ ወደብ አልባ ሀገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡
የኢትዮጵያ ከአሰብ ወደብ የመገለል ሂደት የጀመረው በ1983 ዓ.ም የኢሕአዴግ እና የሕወሓት ኃይሎች አዲስ አበባን፣ የኤርትራው ሻዕቢያ ደግሞ አስመራንና አሰብን ሲቆጣጠሩ ነው።
በወቅቱ ኤርትራ በይፋ ነፃነቷን ከመቀዳጀቷ በፊትና በኋላ ባሉት ጥቂት ዓመታት፣ አሰብ ለኢትዮጵያ “ነፃ ወደብ” ሆኖ እንዲያገለግል ስምምነት ተደርጎ ነበር። ኢትዮጵያም ያለ ቀረጥ ወደቡን ትጠቀም ነበር።
ለኢትዮጵያ ከወደብ መገለል ድብቁ ሴራ ኢትዮጵያን ከበባ ውስጥ ማቆየትና የባህር በር ማሳጣት ቢሆንም፣ ሌላ አጀንዳ ተመዘዘ፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት፣ የኤርትራ ናቅፋን ማስተዋወቅ እና የንግድ ልውውጡ በዶላር ይሁን በብር በሚሉ ጉዳዮች ላይ ባለመስማማት ውጥረቱ ተባባሰ።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው ድብቅ ውጥረት ግንቦት 1990 ዓ.ም ወደ ይፋዊ የድንበር ጦርነት ተቀየረ። ይህ ክስተት የኢትዮጵያን ከአሰብ ወደብ የመገለል ታሪክ የመጨረሻ ምዕራፍ ጻፈ።
ጦርነቱ እንደተቀሰቀሰ በአሰብ ወደብ በኩል ለኢትዮጵያ ይገባ የነበረው የንግድና የነዳጅ መስመር ተቋረጠ።
ሀገሪቱ በአንድ ጀምበር የወጪና ገቢ ንግዷን ሙሉ በሙሉ ወደ ጅቡቲ ወደብ ለማዞር ተገደደች። የኢትዮጵያ መውጣት ለአሰብ ወደብም ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ውድቀት ሆነ። ወደቡ ከኢትዮጵያ ያገኝ የነበረውን ገቢ አጣ፤ የሞቀው ከተማም ባዶ ሆነ።
ኢትዮጵያ ከአሰብ ወደብ በመገለሏ ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የጂኦፖለቲካ ጫና አሳድሯል።
ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ወደብ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የወደብ አገልግሎት ክፍያ ለመክፈል ተገድዳለች።
ከቀይ ባህር በቅርብ ርቀት ላይ ላለች፣ ህጋዊ እና ታሪካዊ የባለቤትነት መብት ላላት እንደ ኢትዮጵያ ላለች ሀገር የባህር በር ማጣት ማለት ግን፣ ሰውን ያለ ሳንባ እየተነፈስክ ኑር እንደ ማለት ነው፡፡
130 ሚሊየን ህዝብ ላላት ሀገር በጅቡቲ ወደብ ላይ ብቻ መደገፍ፣ የኢትዮጵያን ማከናወን ይፈትነዋል፡፡ ለሀገር ደህንነትና ለፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሰላም ሀሳብ አመንጪነት፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሰላም ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ መንገድ የመጠገን እና በጋራ የመልማት ሥራዎችም ተጀመሩ፡፡
ነገር ግን በቀጣናዊ ጫናዎች እና በሻዕቢያ የሴራ ፖለቲካ የተነሳ የአሰብ ወደብ በድጋሚ ለኢትዮጵያ ንግድ ክፍት ሳይሆን ቀረ፡፡
የኢትዮጵያ ከአሰብ ወደብ የመገለል በፖለቲካዊ ውሳኔዎችና በጦርነት ሳቢያ የተከሰተ የታሪክ ጠባሳ ነው።
ይህ መገለል ሀገሪቱን በዓለም ላይ ትልቅ የሕዝብ ብዛት ኖሯት ቀዳሚዋ ወደብ አልባ ሀገር አድርጓታል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ታሪካዊ እጥረት ለመቅረፍ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ማድረጉን ቀጥሏል።
እኛም ሀገራችን የባህር በር እንዲኖራት እናብር፤ ለኢትዮጵያ የማከናወን አቅም የሚሆነውን የባህር በር ባለቤትነት በጋራ እናሳካ እንላለን፡፡