የኤርትራ ሕልውና ሁልጊዜም ኢትዮጵያን ከማዳከም ጋር የተያያዘ ነው – አቶ ጌታቸው ረዳ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኤርትራ ሀገር ሆኖ የመቀጠል ስትራቴጂካዊ ስሌት ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የሕልውና እና የደህንነት ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ኮሌጅ ዓመታዊ የብሔራዊ ደህንነት ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
አቶ ጌታቸው በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ዘላቂ ቀጣናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የታሪክ ስህተቶችን በጥንቃቄ መመርመርና ወቅታዊ የደህንነት ስጋቶችን በስትራቴጂያዊ እይታ መመልከት ይገባል፡፡
ከዚህ በመነሳትም ባለፉት 100 ዓመታት በኢትዮጵያ የተፈራረቁት መንግሥታት መነሳትና መውደቅ ከኤርትራ ጉዳይ አያያዝ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንደነበረው አብራርተዋል።
የአፄ ኃይለሥላሴ፣ የደርግና የኢሕአዴግ መንግሥታት ጉዳዩን የያዙበት መንገድ ለውድቀታቸው የራሱ የሆነ ትልቅ ተፅዕኖ እንደነበረው አስታውሰዋል።
በ1950ዎቹ የነበረውን የፌዴሬሽን ሥርዓት አወቃቀር ያስታወሱት አቶ ጌታቸው÷ እንደ ጸሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ያሉ የቀድሞ አንጋፋ ዲፕሎማቶች የነበራቸውን አርቆ አሳቢነት አብራርተዋል።
በወቅቱ የነበሩ መሪዎች ዋናው ትኩረታቸው የሕዝብን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት፣ ሰላምን ማስፈንና የጋራ ልማትን ማረጋገጥ ላይ መሆን እንደነበረበት ያምኑ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ይህም አቀራረብ በችኮላ ከሚወሰኑ ውሳኔዎች ይልቅ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከር ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ያለመ እንደነበር አስገንዝበዋል።
አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የኤርትራ እንደ ሀገር የመቀጠል ስትራቴጂካዊ ስሌት ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የሕልውና እና የደህንነት ሁኔታ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ታሪካዊ ሒደቶችን በአግባቡ መረዳትና የወደፊት ግንኙነቶችን በጥንቃቄና በስትራቴጂያዊ እቅድ መምራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሶስና አለማየሁ