የሰላም አማራጭን በማይቀበሉ አካላት ላይ አስፈላጊው ርምጃ ይወሰዳል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል አስተማማኝ ሰላምና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ።
የጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ ዓመት 6ኛ የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔ በአዳማ ጨፌ አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የክልሉ መንግሥት ሰላምን ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የወሰዳቸው ርምጃዎች ውጤታማ ናቸው፡፡
በተለይም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማድረግ በተከናወነው ስራ የክልሉ ሕዝብ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ጽኑ ፍላጎት በተግባር ያረጋገጠበት መሆኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡ ዝናብና ፀሃይ ሳይበግረው በምርጫው በነቂስ በመሳተፍ ለአፍራሽ አካላት ግልጽ መልዕክት ማስተላለፉን ነው ያስረዱት፡፡
በክልሉ በተለያየ መልክ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሙከራ ቢደረግም በሰላም ወዳዱ ሕዝብና በጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ ጥረት መክሸፉን አመልክተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ለዘላቂ ለሰላም መስፈን ባለው ጽኑ ፍላጎት መሰረት የቀረበውን የሰላም አማራጭ በመቀበል ወደ ሰላም የመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።
የመንግሥት የሰላም በር አሁንም ክፍት መሆኑን ያረጋገጡት አቶ ሽመልስ ÷ የሰላም አማራጩን ተቀብለው ለሚመጡ ታጣቂዎች በሩ ክፍት ነው ብለዋል።
የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው በጥፋት ተግባራቸው በሚቀጥሉ አካላት ላይ የክልሉ መንግሥት ጠንካራ የሕግ ማስከበር ርምጃ እንደሚወስድ አስገንዝበዋል።
በዚህም በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል መንግሥት በሙሉ አቅሙ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
በአቤል ነዋይ