Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ምክክሩ የሀገርን ሕልውና ለማስቀጠል ወሳኝ ታሪካዊ ዕድል ነው

 

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ አለመግባባቶችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታትና የሀገር አንድነትን ለማጠናከር ዋነኛ መፍትሄ ነው፡፡

የፌደሬሽን ም/ቤት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ በላይ ወዲሾ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ ሀገራዊ ምክክሩ ቀደም ሲል የነበሩ አለመግባባቶችን በኃይል ከመፍታት ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግር ለመፍታት የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ ባሕል የፈጠረ ነው፡፡

ታጥቀው ወደ ጫካ የገቡ አካላት እንኳን የያዙትን አጀንዳ ይዘው በሰላማዊ መንገድ እንዲወያዩ ዕድል የፈጠረና ታሪካዊ መሰናክል የታለፈበት ሒደት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አራሪዮ ሞሲሳ በበኩላቸው ÷ሀገራዊ ምክክሩ ከነበርንበት ችግርና መከራ መውጫ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

ችግር የሚፈጠረውም ሆነ የሚፈታው በሰው መሆኑን ጠቁመው ÷ ሀገራዊ ምክክሩ ጥያቄን በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት መፍትሔ የሚያመላክት መሆኑን አስረድተዋል።

ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት ከታችኛው የትምህርት ተቋማት ጀምሮ በትውልድና በወጣቶች ላይ መሥራት እንደሚገባ ያስገነዘቡት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወንጌል አማኞች ካውንስል ሰብሳቢ ቄስ ጌታሁን ተክሌ ናቸው፡፡

ሰላማዊ አስተሳሰብና በጎ ግንዛቤ ያላቸውን ወጣቶች እንደ አርአያ በመጠቀም ለትምህርት አገልግሎት ማዋል ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ባሳለፍነው ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.