Fana: At a Speed of Life!

ለመላው ኢትዮጵያውያን የተላለፈ መልዕክት

 

በሀገራችን ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተከናወነ ያለውና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው እጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ የሚመካከሩበት ታሪካዊ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ እንዲሳካ ዜጎች ራሳቸውን ከሀሰተኛ መረጃ በመጠበቅ እና በኮሚሽኑ ላይ ሙሉ እምነት በማሳደር ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪ ያቀርባል፡፡

ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረውን ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በተመለከተ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች አማካኝነት ከእውነታ የራቁ መረጃዎችን እያሰራጩ መሆኑን ኮሚሽኑ ደርሶበታል፡፡

ኮሚሽኑ የመናገር ነጻነትን ሙሉ በሙሉ የሚያከብር ገለልተኛ ተቋም እንደመሆኑ ገንቢ የሆኑ ሃሳቦችንና ውይይቶችን የሚቀበል ቢሆንም ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀሰተኛ መረጃዎች እንዳይታለል አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ይገደዳል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ነው። የዚህ ሂደት ስኬት የሚወሰነው ዜጎች በትዕግስት፣ በጥበብ እና በጋራ የኃላፊነት ስሜት ለመሳተፍ በሚያሳዩት የጋራ ቁርጠኝነት ላይ ነው። ይህም እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ሂደቱ ተጀመረ እንጂ ውጤቱ ገና ነው፡፡ ይህንን ውጤት በትዕግስት መጠበቅ ደግሞ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የተጀመረው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ኮሚሽኑ ባወጣቸው የአሰራር ሂደቶች መሰረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህ መሰረት ባለፉት አራት ቀናት ኮሚሽኑ የጉባኤው ተሳታፊዎች የተጣለባቸውን ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ማድረግን ጨምሮ ለሂደቱ ጠቃሚ በሆኑ የእውቀት እና የስነ-ልቦና ዝግጅቶች እንዲያደርጉ መደላድሉን ፈጥሯል፤ ይህም የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው አንድ አካል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ይህ እየሆነ ባለበት አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ኮሚሽኑ ምክክሩን ለመጀመር እክል እንደገጠመው የተሳሳተ መረጃ ሲያሰራጩ ተመልክተናል፡፡

በመሆኑም መሰል የተሳሳቱ መረጃዎች የራሳቸው ዓላማ ባላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ስለሚችሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየእለቱ የሚኖሩ የምክክር ሂደቶችን ኮሚሽኑ ከሚሰጣቸው መግለጫዎችና የምክክሩን ሂደት ለመዘገብ በስፍራው ከተገኙ መገናኛ ብዙኃን ብቻ በመከታተል ራሱን ከተሳሳቱ መረጃዎች በመጠበቅ የምክክሩን ሂደት እንዲደግፍ ኮሚሽኑ ጥሪ ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ሐምሌ 12 ቀን 2018 ዓ.ም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.