በ2018 በጀት ዓመት ከታቀዱት ስትራቴጂክ አቅዶች ከ96 በመቶ በላይ መፈጸም ተችሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በ2018 በጀት ዓመት ከታቀዱት ስትራቴጂክ አቅዶች ከ96 በመቶ በላይ ተሳክተዋል አሉ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ የከተማ አስተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመትና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አፈፃፀም ግምገማ መጠናቀቁን አስመልክቶ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም በምናብ ያየነውን አቅደን ተግተን ፈፅመናል፤ በዚህም ከ96 በመቶ በላይ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል ብለዋል፡፡
ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የ2018 በጀት ዓመት እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አፈፃፀም ግምገማ በስኬት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
በግምገማው የታቀዱ ስትራቴጂክ ግቦችን በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር በተለወጠ የሥራ ባህል ለመስራትና የተለዩ ድክመቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡
ያለፉት አምስት ዓመታት መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተተገበረበት፣ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የሥራ ዕድል የተፈጠረበት ፣ከ60 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት የተፈፀሙበት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ውጤቶች የተገኙበት ስኬታማ ጊዜ እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡