የላቀ ማዕከላዊ ላቦራቶሪው የሠራዊታችንን ሁለንተናዊ የዘመናዊነት ጉዞ የሚያፋጥን ነው – አይሻ መሃመድ (ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) የኢትዮጵያ መከላከያ ዩንቨርሲቲ የላቀ ማዕከላዊ የምርምር ላብራቶሪ የሠራዊታችንን ሁለንተናዊ የዘመናዊነት ጉዞ የሚያፋጥን ነው አሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲው በመከላከያ ትምህርት፣ ምርምርና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ ከፋች እንደሚሆን የታመነበትን የላቀ ማዕከላዊ የምርምር ላቦራቶሪ አስመርቋል፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የላቀ ማዕከላዊ የምርምር ላቦራቶሪው የትምህርት፣ የሳይንስ እና የተቋማዊ አቅም ምዕራፍ የተከፈተበት ታላቅ አጋጣሚ ነው፡፡
ማዕከሉ የረቀቁ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን ከመትከል ባሻገር እውቀትን ወደ ሙያዊ ብቃት፤ ምርምርን ወደ ፈጠራ እንዲሁም ፈጠራን ወደ ተግባራዊ መፍትሔዎች የሚቀይር ነው ብለዋል፡፡
ለዚህ አዲስ የልህቀት ምዕራፍ መከፈት መሠረት የሆነው በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መካከል ያለው ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት፣ የጋራ እምነትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ነው መሆኑን ተናግረዋል።
የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ የወዳጅነት ትስስር ቀደም ሲል ከነበሩት ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ባሻገር አሁን ላይ በሀገራዊ ደህንነት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የተቋማት ዘመናዊነትን ወደሚያጎለብት የላቀ ምዕራፍ መሸጋገሩንም ጠቁመዋል።
ማዕከሉ ከቁሳቁስ ድጋፍ ባለፈ በዕውቀት ሽግግር፣ በሳይንሳዊ ምርምርና በሀገር በቀል የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ላይ የወደፊቱን ትውልድ የሚቀርፅ አዲስ ታሪካዊ አሻራ የሚያኖር መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ላቦራቶሪው የመከላከያ ሠራዊታችንን ሁለንተናዊ የዘመናዊነት ጉዞ የሚያፋጥን ነው ያሉት ሚንስትሯ፥ የቴክኖሎጂና የምርምር መሠረትን የሚያጎለብት እንዲሁም የወደፊት ሀገራዊ ደህንነታችንን በፅኑ መሠረት ላይ የሚጥል ታላቅ ርምጃ ነው ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስቴር የተቋሙን አቅም ለመገንባትና ለማዘመን በተከናወኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግሥት ላደረገው ድጋፍና ያልተቋረጠ ወዳጅነት ሚኒስትሯ እውቅና ሰጥተዋል።
በዓለምሰገድ አሳዬ