የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መግለጫ ዋና ዋና ነጥቦች፡- On Aug 17, 2026 126 አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገ/ሥላሴ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን አሁናዊ ሁኔታ አስመልክተው በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ በመግለጫቸው ያነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡- ባለፉት ቀናት ስምንቱ የአጀንዳ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 16 ተመካካሪዎችን መርጠው ከየቡድኑ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦችን ለማጣጣም ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ይህ የማጣጣም ስራ በምክረ ሀሳቦች ውስጥ ተቃርኖ እና ድግግሞሽን በማስቀረት ወጥ በሆነ መንገድ እንዲቀርቡ የሚያስችል ነው፡፡ በተጨማሪም የየቡድኖቹ ተወካዮች በሌሎች ቡድኖች ስለቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ግንዛቤ ይወስዳሉ፤ እርስ በርስ ይመካከራሉ፡፡ ካሳለፍነው ሀሙስ ጀምሮ ሲከናወን የቆየው ምክረ ሀሳቦችን የማጣጣም ስራ ወሳኝ ስራ ነው፡፡ የምክረ ሀሳብ ማጣጣም ስራው በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል፡፡ ተጣጣመው የሚቀርቡ የስምንቱም ቡድኖች ምክረ ሀሳቦች ለሁሉም ተመካካሪዎች ተመልሰው ይቀርባሉ፡፡ ስምንቱ ቡድኖች የራሳቸውን ምክረ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ቡድኖች ያቀረቧቸውን ምክረ ሀሳቦች ይተዋወቃሉ፤ ግብአት እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ እያንዳንዱ ቡድን በሌሎች ቡድኖች ምክረ ሀሳብ ላይ የሚሰጡት ግብአት ተሰብስቦ የመጨረሻው ሰነድ ይዘጋጃል፡፡ ስምንቱም ቡድኖች ኢትዮጵያን የሚመስሉ ቡድኖች ናቸው፤ በሁሉም ቡድኖች ውስጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይገኛሉ፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ወረዳዎች በስምንቱም ቡድኖች ውስጥ ተወክለዋል፡፡ ዛሬ ከሰዓት በኋላ እና ነገ በምክረ ሀሳቦቹ ላይ ግብአት ከተሰበሰበ በኋላ ከነገ በስቲያ ረቡዕ ዕለት ሁሉም ተመካካሪዎች ያጸድቁታል፡፡ በሒደቶቹ ላይ እየቀረቡ ያሉ ቅሬታዎችን እየመረመርን ውሳኔ እየሰጠን ነው፤ ቅሬታ በቀረበባቸው ቀሪ ጉዳዮች ላይም ውሳኔ እየሰጠን እንቀጥላለን፡፡ ቅሬታዎችን የሚያስተናግድ ኮሚቴ አለ፤ ኮሚቴው አጥንቶ ለኮሚሽነሮች ካውንስል ያቀርባል፤ ካውንስሉ ይወስናል፡፡ በአንዳንድ ወቅት በራሳቸው መግለጫ ያወጡ ወገኖች አሉ፤ የምክክሩ መንፈስ መመካከር ነው፡፡ የተጠናቀሩት ምክረ ሀሳቦች ጉባኤው የተስማማባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ በየትኛውም ሀገር በሚደረጉ ሀገራዊ ምክክሮች ሙሉ በሙሉ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ይስማማሉ አይባልም፡፡ በሀገራችን የተካሄደው የሀገራዊ ምክክር በአብዛኛው ጉዳይ ላይ እየተስማማ ጨርሷል፤ በአብዛኛው ጉዳይ ላይ ተግባብቷል፤ ስለዚህ ደስ ብሎናል፡፡ የደረስንበትን ምዕራፍ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እናበስራለን፡፡ የፈለግነውን መግባባት፤ የፈለግነውን ሰላም ያመጣልናል ብለን እንገምታለን፡፡ በኃይለማሪያም ተገኝ 126 Share FacebookTwitterTelegramWhatsAppEmailViberPrint