Fana: At a Speed of Life!

ማንቼሰተር ዩናይትድ ከቶተንሃም ሆትስፐር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በ6ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ምሽት 1 ሰዓት 30 ላይ ማንቼስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ ቶተንሃም ሆትስፐርን ያስተናግዳል።

በአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ የሚመራው ማንቼስተር ዩናይትድ እስካሁን በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንዱ ብቻ ነው።

በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዶ በሁለቱ ደግሞ አቻ መለያየቱ ይታወሳል።

በአዲሱ የውድድር ዓመት መልካም ጅማሮ ላይ የማይገኘው ማንቼሰተር ዩናይትድ ከተከታታይ 3 ድል አልባ ጉዞ በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማል።

በአሰልጣኝ ሮቤርቶ ዲዘርቢ የሚመራው ተጋጣሚው የሰሜን ለንደኑ ክለብ ቶተንሃም ሆትስፐር የወድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል።

ቶተንሃም ሆትስፐር በዚህ የውድድር ዓመት በሊጉ እስካሁን ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ ተሸንፎ በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

አስቸጋሪ የውድድር ዓመት ጅማሮ ላይ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐር የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት የሚያደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድሮች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ቶተንሃም ሆትስፐር በሶስቱ ድል በማድረግ የበላይነት አለው።

ማንቼስተር ዩናይትድ በአንዱ ሲያሸንፍ በቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ቀን 8 ሰዓት 30 ላይ አርሰናል በሜዳው ኢምሬትስ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።

ሊጉ ለሀገራት ጨዋታ ከመቋረጡ አስቀድሞ በብራይተን ያልተጠበቀ ሽንፈት ያስተናገደው አርሰናል ወደ ድል ለመመለስ ይፋለማል።

ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል በኋላ በ5ኛ ሳምንት ሽንፈት የገጠመው አርሰናል በጨዋታው ድል የሚያደርግ ከሆነ ነጥቡን ወደ 15 ከፍ ማድረግ ይችላል።

በዚህም ማንቼሰተር ሲቲ እሁድ ጨዋታውን እስከሚያደርግ ድረስ በነጥብ ከሊጉ መሪ ጋር የሚስተካከል ይሆናል።

በሊጉ እስካሁን ድረስ አንድም ጨዋታ ካልተሸነፉ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሊድስ ዩናይትድ ያለመሸነፍ ጉዞውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባል።

ሊድስ ዩናይትድ በዚህ የውድድር ዓመት በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በሶስቱ አቻ ተለያይቷል።

ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አርሰናል ሁሉንም በማሸነፍ የበላይነት አለው።

አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ቼልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ቦርንማውዝን ያስተናግዳል።

ባለፉት ሶስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ድል ያልቀናው ቼልሲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።

ተጋጣሚው ቦርንማውዝ በበኩሉ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለማግኘት ይፋለማል።

አስቶን ቪላ ከብሬንትፎርድ፣ ኢፕስዊች ታውን ከፉልሃም እንዲሁም ሰንደርላንድ ከብራይተን በተመሳሳይ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ሌሎች የሊጉ ጨዋታዎች ናቸው።

ዛሬ በሚደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች ዙሪያ ያላችሁን የጨዋታ ውጤት ግምታችሁን አጋሩን።

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.