የኢትዮጵያ ስኬትና የነገ ትውልድ ግንባታ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራት ለዘላቂ ህልውናቸው፣ ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው የሚያደርጉት ጥረት የሚጀምረው ከትውልድ ግንባታ መሰረት ነው።
ሀገርን በጽኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ደግሞ ከሁሉ አስቀድሞ በህፃናት ቀዳማይ እድገት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ተተኪ የሌለው ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
የነገን ብቁ፣ ጤናማና ኃላፊነት የሚሰማውን ዜጋ የመቅረጹ ሂደት የሚጀምረው ከፅንስ እስከ መጀመሪያዎቹ ጥቂት የልጅነት ዓመታት በሚደረግ ሁለንተናዊ እንክብካቤ ነው።
የመንግሥት ሁለንተናዊ የልማት አጀንዳና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከህፃናት እድገት፣ ደህንነትና ደስታ ጋር ተቆራኝተው በጥበብ እየተተገበሩ ይገኛሉ።
በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ እየተተገበረ የሚገኘው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ኢትዮጵያ በዚህ መስክ አህጉራዊ ተሞክሮና አርአያ መሆን መቻሏን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ታሪካዊ ሁነት ነው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች ፎረም ላይ እንደገለጹት÷ በቀዳማይ ልጅነት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ጤናማ፣ ብቁና ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ ግንባታ ወሳኝ ነው።
የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም በቅድመ መደበኛ ትምህርት፣ በጤና እንክብካቤ፣ በህፃናት ማቆያዎችና በወላጆች ስልጠና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ዘመናዊና የተቀናጀ አሰራር ነው።
ይህም አቀራረብ ህፃናት አካላዊ፣ አእምሯዊና ማህበራዊ እድገታቸው የተሟላ እንዲሆን የሚያስችል ሲሆን፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እያከናወነች የምትገኘው ተግባር ትልቅ አድናቆትን አትርፏል።
የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሺቲማ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ÷ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም አፈጻጸም በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርጥ የሚባል ተሞክሮ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ የተገኙት ተግባራዊ ትምህርቶች በናይጄሪያ የተጀመረውን የሥርዓተ ምግብና የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለማሸጋገር ትልቅ ድጋፍ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።
ይህም ምስክርነት ኢትዮጵያ በቀዳማይ ልጅነት ልማት ዘርፍ የዘረጋችው ሥርዓት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የትምህርትና የመማሪያ ምንጭ መሆን መቻሉን የሚያሳይ ነው።
በህፃናት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የነገዋን አፍሪካ ብሩህ የሚያደርግ የህልውና ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ በፅኑ አቋም እየገነባችው ያለው ይህ ሥራ የልጆቿን ህይወት ወደተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ከመሆኑም በላይ ለአህጉሪቱ የተቀናጀና ዘላቂ የልማት መንገድ ማሳያ ሆኖ ያገለግላል።
በመሆኑም የአፍሪካ ከተሞች ይህንን ተሞክሮ በመቀመር ለዜጎቻቸው ምቹና ለህፃናት ደስተኛ ከተሞችን የመፍጠር ጥረታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
በዮናስ ጌትነት