የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የ10 አመት መሪ የልማት እቅዱ ላይ ውይይት እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅዱ ላይ ውይይት እያካሄደ ነው።
ባለስልጣኑ በሎጅስቲክና ባህር ዘርፎችም በቀጣይ 10 ዓመታት ሊሰሩ የታቀዱ ጉዳዮች ላይ እየመከረ ይገኛል።
እቅዱም ኢትዮጵያን በመጭዎቹ 10 ዓመታት በሎጅስቲክ አገልግሎት ከአፍሪካ ቀዳሚ ማድረግ እና ብቁ ባህረኞችን በማቅረብ ከአለም 5 ቀዳሚ ሀገራት አንዷ የማድረግ ራእይ አስቀምጧል ነው የተባለው።
ከጅቡቲ ውጭ በፓርት ሱዳን እና በርበራ ወደብ ያለውን ተጠቃሚነት ማሳደግም ሌላው ይሻሻላል ተብሎ የተቀመጠ ጉዳይ ነው።
የመልቲ ሞዳል አፈፃፀምም አሁን ካለው የተሻለ አካሄድን ማጠናከር፣ የደረቅ ወደብ ቁጥሮችን ወደ 11 ከፍ ማደረግም ይሰራባቸዋል የተባሉ ጉዳዮች ናቸው።
የዘርፉ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት ባለው ውይይት የቴክኖሎጅ አጠቃቀም ችግር፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር ዋና ዋና የዘርፉ ችግሮች መሆናቸው ተገልጿል።
በሎጅስቲክ አገልግሎት መሻሻል የታየባቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ በባህር ዘርፉና ወደብ አጠቃቀም ላይ ሰፊ ችግር አለም ተብሏል።
በሀብታሙ ተክለስላሴ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።