ከተቀባይነት ወደ ሰጭነት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጰያ የኢኮኖሚ ምሰሶ ሆኖ የዘለቀው የኢትዮጰያ ግብርና ለለውጥ ያልተሰራ ይመስል በአዝጋሚ ጉዞ ላይ ቆይቷል፡፡
የዝናብ ወቅት ላይ እና የበሬ ጫንቃ ላይ ተንጠልጥሎ የቆየው የኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ አሁን ላይ የለውጥ ጎዳናን ይዟል፡፡
ባለፉት ስምንት ዓመታት የኢትዮጵያ ግብርና ከቆመበት ተነስቶ ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሻገረችበት እና የረጅም ዘመን ስብራቱን በጽናት መገንባት የጀመረበት አዲስ የህዳሴ መንገድ ላይ ይገኛል።
ይህ ለውጥ በባዶ ተስፋ ላይ የተገነባ ሳይሆን መሬት በረገጡ ትልልቅ መዋቅራዊ ለውጦች የተደገፈ ነው።
ቀደም ሲል በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን በማውጣት ስንዴ ከውጭ የምታስገባዋ ኢትዮጵያ፣ ዛሬ በቆላማ እና ደጋማ አካባቢዎች የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማትን በማሳደግ በስንዴ ምርት ራሷን ችላ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ ጀምራለች።
ከዚህ ቀደም የተበታተነ እና አነስተኛ መሬት የነበራቸው አርሶ አደሮችም በክላስተር እርሻ በመደራጀት ትራክተር፣ ኮምባይነር እና ምርጥ ዘርን በጋራ መጠቀም በመጀመራቸው የምርታማነትቱን መጠንከፍ አድርገውታል።
ከዚህ በተጨማሪም በሌማት ትሩፋት አማካኝነት አቮካዶ ፣አትክልትና ፍራፍሬ ፣ዶሮ ፣ወተት እና የወተት ተዋፅኦ ምርት እድገት እየታየ ነው፡፡
ይህ የኢትዮጵያ የግብርና ሽግግር በዓለማቀፍ ደረጃ ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡
በ1960ዎቹ ህንድ የአረንጓዴ አብዮት በሚል ስትራቴጂ ምርጥ ዘርን እና የመስኖ አጠቃቀምን አዋህዳ ረሃብን እንዳሸነፈች ሁሉ፣ ኢትዮጵያም የመስኖ ስንዴን በስፋት በመጠቀም የብሔራዊ ምግብ ዋስትናዋን እያረጋገጠች ትገኛለች።
የተመዘገቡትን ስኬቶች ዘላቂ ለማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ዘመናዊ የውሃ አጠቃቀም ዘዴዎችን ማስፋፋት፣ የማዳበሪያ እና ግብአቶች አቅርቦትን ማረጋጋት፣ እንዲሁም ከምርት ስብሰባ በኋላ የሚፈጠሩ ብክነቶችን መቀነስ ላይ እየተሰራ ቢሆንም በቀጣይም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው።
ባለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ ግብርና ላይ የታየው ለውጥ ትክክለኛ ፖሊሲ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የህዝብ ቁርጠኝነት ሲገናኙ የዘመናት ታሪክን በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀየር እንደሚቻል አመላካች ነው፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ዛሬ የምግብ ዋስትናችን ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣዩ ትውልድ እና ለቀጣናው ሀገራት ትልቅ የልማት ተምሳሌት ሆኖ ቀጥሏል።
#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ
በእመቤት ሲሳይ